በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰ ውጊያና የምግብ ዕጥረት ብዙ ሺህ ህዝብ ወደ አጎራባች ሃገሮች እየተሰደደ ነው


ሰሜን ባህር ኤል ጋዛል፣ ደቡብ ሱዳን
ሰሜን ባህር ኤል ጋዛል፣ ደቡብ ሱዳን

ደቡብ ሱዳን ውስጥ ካሁን ቀደም ሰላማዊ በነበሩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ውጊያና ከባድ የምግብ ዕጥረት ምክንያት ብዙ ሺህ ህዝብ ወደ አጎራባች ሃገሮች መሰደዱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታወቀ። እኛም ሆንን ሌሎች የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅቶች ለስደተኞቹ ህይወት አድን አገልግሎት የምናውለው ገንዘብ እየተሟጠጠብን ነው ሲል ዩኤን ኤች ሲ አር (UNHCR) አስጠንቋል።

የደቡብ ሱዳን ውጊያ ከተጀመረ ወዲህ ቀዬውን ጥሎ የተሰደደው ህዝብ ቁጥር ከሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን በላይ ሲሆን ከስድስት መቶ ሰባ ሺህ የሚበልጡት በአጎራባች ሃገሮች ተጠልለዋል።

ውጊያው ቀድሞ ሰላማዊ ወደነበሩት ሰሜናዊ ባህር ኤል ጋዛል እና ዋራፕ ክፍላተ ሃገር እየተዛመተ በመሆኑ የተ.መ.ድ. የስደተኞች ጉዳይ ኮሚስን ወደ ሁሉም አጎራባች ሀገሮች የሚነጉደው ስደተኛ ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቋል።

ሁኔታው ተቀባዮቹ ሀገሮች ላይ ከባድ ሸክም እየፈጠረ መሆኑንም ገልጾ እኛም ሆንን ሌሎችም የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች ለስደተኛው ህይወት አድን አገልግሎቶች የምናውለው ገንዘብ እየቸገረን ነው ብሏል።

ካለፈው ጥር ወር ወዲህ ቁጥራቸው ሃምሳ ሁለት ሺህ የሚጠጋ ወደ ሱዳን አቋርጠዋል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ኤሪያን ሩሜሪ እንዳሉት ወደ ዩጋንዳ የሚሰደዱትም ቁጥር ጨምሮ በየቀኑ ስምንት መቶ ስደተኛ እየገባ ነው። ቁጥሩ ከየትኛውም ሀገር የሚበልጥ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን የምታስተናግደው ኢትዮጵያ ስትሆን ወደ ሁለት መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ስደተኞች ይዛለች።

ከደቡብ ሱዳን የተሰደደ ህጻን በጋምቤላ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ /ፋይል ፎቶ/
ከደቡብ ሱዳን የተሰደደ ህጻን በጋምቤላ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ /ፋይል ፎቶ/

ታዲያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ለረጅም ጊዜ እጅግ በጣም ጥቂት እንደነበር የዩኤን ኤች ሲ አርዋ (UNHCR)ቃል አቀባይ ሩሜሪ አስታውሰው በቅርብ ሳምንታት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። አብዛኞቹ ልጆች መሆናቸውን አመልክተዋል።

"ኢትዮጵያ ከሚገቡት አዲሶቹ ስደተኞች ውስጥ የሚበዙት በምስራቅ ሱዳን ፖቻላ ከሚካሄደው የብሄረሰቦች ውጊያ ሸሽተው ለብቻቸው የሄዱ ወይም በመካከል ከወላጆቻቸው የተለያዩ ናቸው። ብዙዎቹ ለብዙ ቀናት በጫካው ውስጥ ኳትነው ነው ኦኩጎ የደረሱት።"ብለዋል።

ወደ ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሰሜን ምስራቅ ኬንያ እና መካከለኛ አፍሪካ ሪፑብሊክ የሚገቡትም ቁጥር አድጓል። በዓመቱ መጀመሪያ ኬኒያ የገቡት ቁጥር በአማካይ በወር አንድ መቶ እንደነበሩ ያወሳው ዩ ኤን ኤች ሲ አር (UNHCR) ባለፉት ሁለት ወራት አሻቅቦ በሳምንት ሶስት መቶ ሃምሳ ስደተኞች እየገቡ መሆኑን አውስታቋል። ደቡብ ሱዳናውያኑ አገር ጥለው የሚሰደዱት ውጊያ፣ እጅግ ከባድ ድርቅ እና የኑሮ ወድነቱን በመሸሽ መሆኑን ይናገራሉ።

ሊሳ ሽላይን (Lisa Schlein) ከጄነቫ ያጠናቀረችውን ዘገባ ቆንጂት ታየ አቅርባዋለች፣ ከድምጽ ፋይሉ ያድምጡ።

በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰ ውጊያና የምግብ ዕጥረት ብዙ ሺህ ህዝብ ወደ አጎራባች ሃገሮች እየተሰደደ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:40 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG