በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሪያክ ማቻር ቃለ-መሃላ ፈፀሙ


“እኔ ሪያክ ማቻር በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንትነት የደቡብ ሱዳን ሪፑብሊክን በታማኝነትና በሃቅ ላገለግል በኃያል አምላክ እምላለሁ።”

ዶ/ር ሪያክ ማቻር ማክሰኞ፤ ሚያዝያ 18/2008 ዓ.ም ዋና ከተማዪቸው ጁባ ገብተው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

ማቻር በሃገሪቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው የገበቡበት ግዴታና በብርቱ የማሉበት ቃል ዘርዘር ያለና የሚጠበቅባቸውን በትኖ የሚያስገነዝብ ነው።

ለደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ያላቸውን ፍፁም ታማኝነት ያስረግጣል፤ ልማትን ለማቀላጠፍ፤ የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ ሕይወት በተሻለ ገፅታው ለመለወጥ፤ በትጋት ለመሥራትና በታማኝነት ለማገልገል፤ ለሕገመንግሥቱን ታዛዥ ሊሆኑ፣ ሊያከብሩትና ከአደጋ ሊጠብቁት፤ ለሕግ ተገዢ ሊሆኑ፤ የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ አንድነት ሊጠብቁና ሊንከባከቡ፤ ያልተማከለ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት አሠራርን ሊያፀኑ፤ የደቡብ ሱዳንን ልዕልናና ክብር ሊጠብቁ ነው የኃያል አምላክን ስም ጠርተው የማሉትና አዲሱን ሥራቸውን የጀመሩት።

እንግዲህ ማቻር በድጋሚ ጁባ ናቸው፤ በድጋሚም ቤተመንግሥቱ ውስጥ ናቸው፤ እንደገናም የሃገሪቱ አንደኛ ምክትል ርዕሰ-ብሔር ናቸው።

ማቻር ቀድሞም’ኮ የፕሬዚደንት ኪር ምክትል ነበሩ። እስከዛሬ ማናቸውም እንዲህ ብለው ያልተናገሩት አንዳች ነገር መካከላቸው ተፈጠረ፤ ሰላም ደፈረሰ፤ ፍቅር ጠፋ። በሃምሌ 2005 ዓ.ም (የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ) ማቻር ከቤተመንግሥቱ ተባረሩ። በአራት ወራቸው ታህሳስ ላይ ብረት አነሱና ሸፈቱ።

የማቻር ጁባ መግባትና የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን መረከብ በመንግሥቱና በርሣቸው ሲመሩ የቆዩት አማፂያን ለሰላሣ ወራት ተዘፍቀውበት የቆዩትን የርስ በርስ መቆራቆስ ያበቁ ዘንድ ባለፈው ዓመት የፈረሙትን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል የሚል ተስፋ ፈንጥቋል።

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንታዊ ቤተመንግሥት ከተከናወነው የቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓት በኋላ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ባደረጉት ንግግር ዕለቱ ለሀገራቸው የሰላምና የመረጋጋት ጅማሮን እንደሚያበስር ተናግረዋል።

“እኔ በግሌ ለወንድሜ ሪያክ ማቻር ቡድን ጁባ ላይ የሞቀ አቀባበል ሳደርግ ከፍ ያለ ደስታ እየተሰማኝ ነው፡፡ ዛሬ ጁባ ላይ እያከበርን ያለነው የጦርነቱ ማብቂያና የሰላምና የመረጋጋት ጊዜ መጀመሪያ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም” ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር።

የፈረሙትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ሕዝባቸውና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚያምን፤ ተስፋ እንዳልቆረጠባቸው ፕሬዚዳንት ኪር ተናግረዋል። ሪያክ ማሻር ሥልጣናቸውን የተረከቡ በመሆኑም የብሄራዊ አንድነት መንግሥት እንደሚመሠርቱ አመልክተዋል ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር።

ሁለቱም መሪዎች ደስታቸውን ቢገልፁም፤ ስለብዙ ተስፋ ቢናገሩም መንገዳቸው አልጋ ባልጋ እንዳልሆነ ግን ፕሬዚዳንቱ ሳያስታውሱ አላለፉም።

“ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ ገና ያልተፈቱ ጉዳዮች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን በመግባባት እንፈታቸዋለን” ብለዋል።

ማቻርም ከፕሬዚደንት ኪር ጋር ተባብረው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

ጦራቸው እኮ አንዳች በጎ ነገር ለሁለቱም አልፈየደም። ለሕዝባቸው ያመጣው መከራ፤ ሞትና ረሃብ ብቻ ነው። አሥሮች ሺሆች ተገደሉ። ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰው ተሰደደ፤ የየጎረቤት እጅ ተመልካች ሆነ።

ሚስተር ማቻርን ያሣፈረው አይሮፕላን ዛሬ ጠዋት ጁባ የገባው ከአንድ ሣምንት በላይ ዘግይቶ ነው። ለምን? ጁባ የሚሠፍረው ጋሻ ጃግሬ ሠራዊታቸው በሚይዘው ትጥቅ መጠን ላይ በመንግሥቱና በያኔዎቹ አማፂያን መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ ነበር። ለማንኛውም ደመናው የገፈፈ ይመስላል፤ የጁባ አየር ዛሬ በተሻለ ተስፋ ተሞልቶ ውሏል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር ግን የዶ/ር ሪያክ ማቻር ወደ ጁባ የመመለስ ጉዳይ እንዲህ ከባድ የሆነው በሀገሪቱ በፈሰሰው ደም ምክንያት ያለው ያለመታማመን ድባብ ነፀብራቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች የጋራ ልማት ትብብር ተቋሙ - ኢጋድ ስምምነት የተፈረመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት፣ የአፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ ባደረጉት ተደጋጋሚ ጫና ምክንያት እንደነበር አመልክተዋል።

በስም የሚጠቀሱ የአፍሪካ ሀገሮችም በደቡብ ሱዳን መንግሥትና በሪያክ ማቻር ወደ ጁባ መመለስን በሚመልከት የመፍትሄ ግልግል ላይ ባለመድረስ ጉዳይ ላይ ትዕግስት አይኖረንም በማለት በጥብቅ ሲያሳስቡ መቆየታቸውንና የደቡብ ሱዳን ህዝብን ሊጠቅም የሚችል ተግባር ሲከናወን በውጭ ተፅዕኖ መሆን እንደሌለበት ማስገንዘባቸውንም አምባሣደር ፓወር ገልፀዋል።

ከብዙ ወራት ብጥብጥ፤ ከብዙ ወራት ደም መፍሰስ በኋላ ዛሬ ለደቡብ ሱዳን በጎ ቀን የዋለ ይመስላል - ከግራም ከቀኝም እንደሚሰማው።

ሪያክ ማቻር ቃለ-መሃላ ፈፀሙ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:24 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG