ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ያልታየ በተባለው በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ከስድስት ሚልዮን በላይ ሕጻናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፤ ሲል ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት Save the Children አስታወቀ።
በድርቅ በተመቱት አካባቢዎች ተዘዋውረው የጉዳቱት መጠን የተመለከቱት አዲስ የተሰየሙት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄለ ቶርኒንግ ሽሚዝ (Helle Thorning-Schmidt) ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት ቃል፤ ድርቁ ባጠቃቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ቤተሰቦች ምግብና ውሃ ፍለጋ ከቀያቸው ርቀው ለመሄድ እየተገደዱ መሆናቸውን ገልጠዋል።
ሕጻናቱ እጅግ በጠናው የምግብ እጥረት ሳቢያ ለከፋ ስቃይና እንዲሁም ድርቁን ተከትሎ ለሚከሰቱ የተለያዩ ውሃ-ወለድ በሽታዎች እንዳይጋለጡ፤ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፈጥኖ ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል፤ ሲሉም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አሳስበዋል።
“እልቂቱን ለመታደግ አሁንም ጊዜው አልረፈደም፤” ሲሉ ነው፤ ያንዣበበውን አደጋ አሳሳቢነት አጽንኦት በመስጠት የሴቭ ዘ ችልድረን (Save the Children) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄለ ቶየነን ሽሜድ፥ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅና ረሃብ አስመልክቶ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ የቋጩት።