ናይሮቢ —
በኬንያው የምርጫ ኰሚሽን ውስጥ ለውጥ እንዲደረግና የኰሚሽኑ አባላትም ከሥራቸው እንዲነሱ የሚጠይቅ፣ በአንድ ወር ውስጥ ዛሬ፣ ፫ኛውን ሰኞ መያዙ ተገለጸ። በዚህም፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች ናቸው ናይሮቢ ውስጥ የተሰባሰቡት።
አብዛኛዎቹ የተቃዋሚው ጣምራ አባላት የሆኑበት ሰላማዊ ሰልፈኞች፣ የአገሪቱን የምርጫና የድንበር ኰሚሽን፣ "ለገዢው ፓርቲ ያደላ ነው" ሲሉ ይከሳሉ። እናም ነፃ፣ ትክክለኛና ተጠያቂነት ያለው ምርጫ ማካሄድ የሚችል ኰሚሽን አይደለም ይላሉ።
የተቃዋሚው መሪና "ለውጥ የሌለበት ምርጫ አይካሄድም" የሚል መፈክር ያነገበውን ሰልፍ የሚያስተባብሩት ሴናተር ጄምስ ኦረንጎ "ይህ የምርጫ ኰሚሽን እስካለ ድረስ፣ ሀቀኛ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም" ማለታቸው ተሰምቷል።
ፖሊስ ጥበቃውን አጠናክሮ መተላለፊያዎችን ስለዘጋ፣ ሰልፈኞቹ በዛሬው ቀን፣ ንግግሮች ወደሚደረጉበት አካባቢ መዝለቅ እንዳልቻሉ ተገልጧል። አንድ ሰልፈኛ በፖሊስ ተተኩሶበት በመቁሰሉ ወደ ሆስፒታል መውሰዳቸውን ሴናተር ኦሬገን ተናግረዋል።
ኬንያ፣ እአአ በመጪው 2017 ዓ.ም ነሐሴ ወር፣ ፕሬደንታዊና ምክር ቤታዊ ምርጫዎችን ለማድረግ ማቀዷ ይታወቃል።