በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት በናይሮቢው የዓለም የንግድ ድርጅት ጉባዔ ስብሰባ ላይ ፀድቋል


Kenya WTO Conference
Kenya WTO Conference

ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ላይ ሲካሄድ የሰነበተው በእግሊዝኛ ስሙ ምኅፃር (WTO) እየተባለ የሚታወቀው የዓለም የንግድ ድርጅት ጉባዔ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቀቀ። ድርጅቱ በዘንድሮው ስብሰባ የላይቤርያንና የአፍጋንስታንን የአባልነት ጥያቄ አጽድቋል።

ኬንያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የሆነችው የዛሬ ሃያ ዓመት በ1988 ዓ.ም የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ባሠናዳችውና ባስተናገደችው የድርጅቱ አሥረኛ ጉባዔ ላይ 162 አባል ሀገሮች ተሣትፈዋል። የዓለም የንግድ ድርጅት ጉባዔውን በአፍሪካ ምድር ሲያደረግ የዘንድሮው የመጀመሪያ ነው።

በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሃገሮቹ ከ 1 ትሪልዮ ዶላር በላይ የሚገመት የንግድ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በልማት ወደፊት ያልገፉት የድርጅቱ አባል ሃገሮች በድርጅቱ ሊደገፉ በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ተስማምተዋል።

በተለይ ምጣኔ ኃብታቸው እጅግ ኋላ ቀር የሆነ አባል ሃገሮችን ይደጉማል የተባለው የነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትም በዚሁ በናይሮቢው ስብሰባ ላይ ፀድቋል።

በስምምነቱ የድርጅቱ አባል የሆኑ አፍሪካ ሃገሮችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የብራንድ ኬንያ ቃል አቀባይ ሼይላ ኦቺኤንግ ገልፀዋል።

በመረጃ ቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ቀረጥ አሁን ተነስቷል። ይህ ማለት ደግሞ ለአፍሪካ ሃገሮች ዕድገት ይበጃል። ምክንያቱም እነዚህ መሣሪያዎች በአንድ ሃገር ዕድገት ላይ ትልቅ ድርሻ አላቸውና ነው። እነዚህን መሣሪያዎች በብዛት ካገኘን የሥራ አፈፃፀማችን ይሻሻላል፤ የሥራ ፈጠራም በአፍሪካ ውስጥ እየተስፋፋ ይመጣል።

የዓለም የንግድ ድርጅት በዚህ የዘንድሮው ስብሰባው ላይቤሪያንና አፍጋንስታንን በድርጅቱ አባልነት የተቀበለ ሲሆን እዚያው መድረክ ላይ የተገኙት የላይቤርያ ፕሬዘደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ሃገራቸው ከድርጅቱ አባልነት ልታገኝ ያሰበችውን ተናግረዋል።

“የዚህ ድርጅት አባል ለመሆን የፈለግነው ትናንሽ የንግድ ተቋሞቻችንን ለማጎልበት ነው፤ በተለይ ወደ እንዱስትሪ እያደጉ የሚገኙትን። እንደማምነውም የላይቤርያ መንግሥት እያደረገ ባለው የድጋፍ ጥረት ላይ ከድርጅቱ የምናገኘው ድጋፍ ሲጨመር ይህን ዓላማችንን በርግጥ ያሳካልናል”ብለዋል።

ይህ 10ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት አባላት ጉባዔ ስለ ምግብ ዋስትናም የመከረ ሲሆን ስብሰባው በተካሄደበት የኬንያ ዓለምአቀፍ ጉባዔ ማዕከል - ኬአይሲሲ ፊትለፊት የተሰበሰቡ ግዙፍ ቁጥር ያላቸው ተሟጋቾችና ተቃዋሚዎች “ለዓለማችን ፍትህ ያለበት የንግድ ሥርዓት ያስፈልጋል” በማለት ድምፃቸውን አሰምተዋል።

XS
SM
MD
LG