በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ የሠላም ሥምምነቱ ትግበራ ላይ ይበልጥ እንድትሠራ ብሊንከን አሳሰቡ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

የኢትዮጵያና አሜሪካ ግኑኝነት ወደ ነበረበት መልካም ሁኔታ ከመመለሱ በፊት መንግሥት ከህወሓት ጋር የደረሰውን የሰላም ሥምምነት በመተግበር ረገድ የተሻለ አፈጻጸም እንዲያሳይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን አሳስበዋል።

ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አለመፈጸማችውን ማረጋገጥና ለሁለት ዓመት የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ ሁሉን አካታችና ተአማኒነት ያለው የሽግግር ፍትህ ሥርዓት እንዲፈጠር ብሊንከን ጠይቀዋል።

“ይህ የሚሆን ከሆነ ከኢትዮያ ጋር በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች መስክ ያለን ትብብር ወደፊት ይራመዳል” ሲሉ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ከተወያዩ በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተደረገው ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕይወት ቀጥፏል።

ከጦርነት በኋላ ላለባት የመልሶ ግንባታ ሥራ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልጋት ኢትዮጵያ፣ ከአሜሪካና ሌሎችም አገሮች የኢኮኖሚና ድጋፍ ትሻለች ሲል የአሶስዬትድ ፕረስ ሪፖርት አመልክቷል። በስፋት ተፈጽሟል የተባለውን የመብት ጥሰት በተመለከተ መንግሥት ፈጻሚዎቹን ተጠያቂ ያደርጋል ወይ የሚለው ጥያቄ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ አሳስቧል ሲል ሪፖርቱ አክሏል።

በተመድ የተቋቋመውን አጣሪ ኮሚሽን እንደማይቀበል የኢትዮጵያ መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል።

ብሊንከን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ባለፈው ጥቅምት የሰላም ሥምምነቱን ከፈረሙት የኢትዮጵያ መንግሥት ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ ሬድዋን ሁሴን እና ከህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ጋር የሥምምነቱ አፈጻጸም የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ መወያየታቸው ታውቋል።

የተኩስ ድምጽ ስለመቆሙ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትት፣ የአገልግሎቶች መመለስ እንዲሁም የህወሓት ከባድ መሣሪያ ትጥቅ መፍታትና የኤርትራ ኃይሎች መውጣትን በተመለከተ ተነጋግረዋል ሲል የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አምባሳደር ሬዋን ሁሴንና አቶ ጌታቸው ረዳ ሥምምነቱን ሙሉ ለሙሉ በመተገበርና ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድና ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ መገንዘባቸውን ተናግረዋል ሲል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።

የህወሓት ጦር ትጥቅ መፍታት፣ መበተንና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም መፍጠርና ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ ማድረግ አስፈላጊነት ላይም ተነጋግረዋል ብሏል መግለጫው። ሁለቱ ወገኖች በትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም አስፈላጊነት ላይም ተነጋግረው፣ ተጠያቂነትን ማስፈንና የሽግግር ፍትህ በማቋቋም እንዲሁም ለሠላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በተመለከተ ተወያይተዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ 331 ሚሊዮን አዲስ ሰብዓዊ እርዳታ እንደመደበች ብሊንከን በአዲስ አበባ ቆይታቸው አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG