በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንከን በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ተጠየቀ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

ነገ መጋቢት 6/2015 በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉት የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በሚኖራቸው ውይይት ወቅት በአገሪቱ ለተፈጸሙ ሰቆቃዎች ተጠያቂነት የሚኖርበትን ጉዳይ በተመለከተ ዋና የውይይት አጀንዳቸው እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች ጥያቄውን ያቀረበው ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ቢሮው በኩል ዛሬ ማለዳ ባወጣው መግለጫ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ነገ በሚያደርጉት ጉብኝት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማሻሻልን በተመለከተ እንደሚወያዩ ይጠበቃል ያለው የሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ፣ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊ ዕርዳታን በተመለከተ በቂ መሻሻል ተደርጎ እንደሁ እየተነጋገረበትና እየገመገመ ነው ብሏል። ይህም መግለጫው እንዳለው፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ አስፈላጊ ነው።

በዋሺንግተን ዲሲ የመብት ድርጅቱ ዲሬክተር የሆኑት ሳራ ያገር እንዳሉት “ከሁለት ዓመታት በላይ ለሆነ ግዜ በትግራይና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች የደረሱ ሰቆቃዎችና እየተፈጸሙ ያሉ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገባ ታውቃለች።”

ሳራ ያገር በተጨማሪ እንዳሉት “የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የሚያደርጉት ጉብኝት ሁሉም በጦርነቱ የተሳተፉትን ኃይሎች ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ አሜሪካ ግፊት እንደምታደርግ ለማሳወቅ አጋጣሚውን የሚፈጥር ነው።”

“ከእአአ 2020 ጀምሮ በተፈጸሙት የጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በቁጥር ለማስቀመጥ አስቸጋሪ የሆነ ብዛት ያላቸው ሰዎችና ማኅበረሰቦች አሁንም ስቃይ ላይ ናቸው” ሲል የሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ አመልክቷል። የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ቡድኑ በመግለጫው አያይዞም፣ እነዚህ ተጎጂዎች እንደ አሜሪካ ያሉ የኢትዮጵያ አጋሮች ፍትህን ለማስፈንና ካሳን ለማግኘት ግፊት እንዲያደርጉ ይጠብቃሉ ብሏል።

“አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ተሟላ ደረጃ ከመድረሱ በፊት እውነተኛ የሆነ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ብሊንከን ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ግልጽ ማድረግ አለባቸው” ብሏል ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው።

“ፍትህ የሌለበትና ሁኔታና፣ የሁከት አዙሪቱ እና በህግ ተጠያቂነት ያለመኖር የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰብዓዊ መብት ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ያዳክመዋል “ ሲል የሰብዓዊ መብት ቡድኑ መግለጫውን ደምድሟል።

የብሊንከንን የኢትዮጵያ ጉብኝት አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ከሶስት ቀናት በፊት ለዜና ሰዎች በሰጡት መግልጫ ብሊንከን በኢትዮጵያና ኒዠር የሚያደርጉት ጉብኝት ሃገራቸው ለአፍሪካ እየሰጠች ያለውን ትኩረት የሚያመላክት መሆኑን አስታወቀዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን ባለፈው ታኅሣስ የአፍሪካን መሪዎች ዋሺንግተን ዲሲ ላይ ማስተናገዳቸውን ሞሊ ፊ አስታውሠው፣ በርካታ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናትና ዜጎች አፍሪካን መጎብኘታቸውን፣ ከመካከላቸውም ቀዳሚዊ እመቤት ጂል ባይደን፣ የገንዘብ ሚኒስትሯ ጃኔት የለን፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። በሁለቱ ወገኖች በኩል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና ለማስፋት ሌሎች በርካታ ባለሥልጣናትም ወደ አህጉሪቱ እንደሚሄዱ ሞሊ ፊ አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG