በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሞሊ ፊ ስለ ብሊንከን ጉብኝት


የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በመጭው ሣምንት የሚያደርጉት የኢትዮጵያና የኒዠር ጉብኝት ሃገራቸው ለአፍሪካ እየሰጠች ያለችውን ትኩረት የሚያመላክት መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ አስታወቁ።

ሚስ ፊ የሚኒስትሩን ጉብኝት አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች በቴሌኮንፍራንስ በሰጡት ማብራሪያ ፕሬዚዳንት ባይደን ባለፈው ታኅሣስ የአፍሪካን መሪዎች ዋሺንግተን ዲሲ ላይ ማስተናገዳቸውን፣ ብዙ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናትና ክቡራን ዜጎች ወደ አፍሪካ መሄዳቸውን፣ ከመካከላቸውም ቀዳሚት እመቤት ጂል ባይደን፣ የገንዘብ ሚኒስትሯ ጃኔት የለን፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ እንደሚገኙበት አስታውሰዋል። ሌሎች ብዙ ባለሥልጣናትም ያንን ግንኙነት ለማጠናከርና ለማስፋት እንደሚሄዱ ፊ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲወርድ ብሊንከን ሥራቸውን ከጀመሩ አንስቶ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውን ያመለከቱት ፊ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተደረጉ ጥረቶች ባለፈው ጥቅምት 23 ፕሪቶሪያ ላይ ለተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ ቁልፍ ሚና መጫወቷን ገልፀዋል። የአሁኑ የብሊንከን ጉብኝት ያ ሰላም የሚጠናከርበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላት ሞሊ አስታውሰው “የራሳቸውን ዜጎች ለማሳደግ፣ እንዲሁም በቀጣናው ጉዳዮች ውስጥም በኃላፊነት መንፈስ በመሣተፍ እጅግ ጠቃሚ ተግባር እያከናወኑ ነው” ብለዋል። “በመሆኑም - አሉ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ በመቀጠል - እኛም ግዝፈታቸውንና ያላቸውን ተፅዕኖ የሚመጥን አፍሪካ ውስጥ ያሉንን ጥቅሞችና ለአህጉሪቱ ያለንን ቁርጠኛነትም የሚተካከል ግንኙነት መፍጠር እንፈልጋለን።”

“ሆኖም ያ ግንኙነት ወደፊት እንዲገፋ የቅርቡን ጦርነት ጨምሮ ሃገሪቱን በብዙ አሥርት ዓመታት ወደኋላ ከዘፈቋት የጎሣ ሁከቶች መውጣት አለባት” ብለዋል ፊ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለዩኤስ - አፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ዋሺንግተን ተገኝተው በነበረ ጊዜ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስርት ብሊንከንና ከብሄራዊ የፀጥታ አማካሪው ጄክ ሱለቫን ጋር ‘መልካም’ ያሏቸውን ውይይቶች ማድረጋቸውንና ከዚያ በኋላም የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር በተከታታይ እየተገናኙ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

የሚኒስትር ብሊንከን የመጭው ሣምንት ጉብኝት ፀቡን ባስቆመው ስምምነት ውስጥ ቁልፍ የአመራር ሚና ለተጫወቱት ምሥጋና ለማቅረብና አዲስና አዎንታዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከርም መንገድ ለመክፍረት የታሰበ መሆኑ ሚስ ፊ አመልክተዋል።

የኤርትራ ወታደሮች በብዙ የወሰን አካባቢዎች አሁንም እንዳሉና የአማሪአ ሚሊሽያም ሰፊ የሆነ አካባቢ ምዕራብና ደቡብ ትግራይ ውስጥ ይዘው እንደሚገኙ እርዳታ አቅራቢዎችና ዲፕሎማቶች እንደሚናገሩ፣ ስለዚህ ጉዳይ እርሳቸው የሚያቁት ይኖር እንደሆነና ብሊንከንም በዚህ ላይ ሊያደርጉ ያሰቡት ሥራ እንዳለ የተጠየቁት ሞሊ ፊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጓቸው የቀደሙ ውይይቶች ጉዳዩን ማንሳታቸውን ተናግረዋል። እስከሚያውቁት ድረስም ውጊያው ሰሜን ትግራይ ውስጥ መቆሙን፣ ግዙፍ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ወታደሮችም ከሰሜን ትግራይ መውጣታቸውን በስምምነቱ መሠረት የተቋቋመው የአፊሪካ ኅብረት የክትትልና አረጋጋጭ አካል ማረጋገጡን ገልፀዋል።

ሰብዓዊ እርዳታም ግጭት ወደጎዳቸው የሰሜን ማኅበረሰቦች ሁሉ እየደረሰ መሆኑን፤ ትግራይን እጅግ በጎዳ ሁኔታ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶች እንደገና መጀመራቸውን ማስተዋላቸውንም የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አንድ ሥራ ላይ ያለ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኒዠርን ሲጎበኝ አንተኒ ብሊንከን የመጀመሪያው እንደሚሆኑ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG