በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ መርዛማ ቅራኔዎችንና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ብሊንከን ተናገሩ


በኢትዮጵያ መርዛማ ቅራኔዎችንና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ብሊንከን ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:57 0:00

በኢትዮጵያ መርዛማ ቅራኔዎችንና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ብሊንከን ተናገሩ

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ጭቆናዎችን እንደምታውቅ ገልጸው፣ እነዚህ ችግሮች በሽግግር ፍትህ እልባት ሊያገኙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እንደምታደርግ የገለጹት ብሊንከን፣ ለሰብዓዊ አገልግሎት የሚውል 331 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍም ይፋ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና፣ ኢትዮጵያ ወደ አጎአ እድል ተጠቃሚነት እንድትመለስ ስምምነቱን የመፈጸም ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አንተኒ ብሊንከን፣ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከምክትላቸው ደመቀ መኮንን እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ውይይታቸውን በማስመልከት ምሽት ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ብሊንከን፣ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለማስወገድ መርዛማ ላሏቸው ቅራኔዎችና ለጎሳ መከፋፈል ችግሮች መፍትሔ ማምጣት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በሽግግር ፍትህ ሊተገበር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

"ኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ፍትህ ሂደት ለማካሄድ በገቡት ቃል መሰረት እንዲያካሂዱ እናሳስባለን። ይህም እርቅንና ተጠያቂነትን የሚያካትት ሊሆን ይገባል፡፡" ያሉት ብሊንከን "መርዛማ ቅራኔዎችን እና የጎሳ መከፋፈልን ማስወገድ፣ በሰሜን፣ በኦሮሚያም ይሁን በየትኛውም አካባቢ ያለውን የፖለቲካ እና ብሄር ተኮር ግጭቶችን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ በዚህ ጥረት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ አጋር እንደመሆኗ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡" ብለዋል።

ኢትዮጵያ እየተጋፈጠቻቸው ያሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ደግሞ፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንቅፋት መሆናቸውን የጠቀሱት ብሊንከን፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ዩናይትድ ስቴትስ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ገልጸው 331 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የሰብዓዊ ድጋፍም ይፋ አድርገዋል፡፡

"ከግጭት፣ ከድርቅ እና ከምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ በመነጨ፣ ኢትዮጵያ ባጋጠሟት የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት ዘላቂ ሰላምን መገንባት በጣም ውስብስብ እየሆነ ነው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደገለጽኩት፣ ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ ቀዳሚ ለጋሽ ሀገር ነች፡፡ ከ2020 ጀምሮ ለሰብዓዊ ድጋፍ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ አሁንም ኢትዮጵያውያንን በዋና አጋርነት መደገፋችንን እንቀጥላለን፡፡ ዛሬ ለአስቸኳይ የምግብ እና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ተጨማሪ 331 ሚሊዮን ዶላር ይፋ አድርገናል፡፡ ይህም በግጭት እና በድርቅ ለተጎዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚውል ነው፡፡" ብለዋል

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈና ሌሎች በርከታ ኢሰብዓዊ ተግባራትንም እንደተፈፀሙበት ያብራሩት የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማቆም የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም፣ ብሊንከን ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ አፍሪካ ችግሮቿን በራሷ እንደምትፈታና አፍሪካዊ መፍትሔዎች ልዩነት እንደሚፈጥሩ የ21ኛው ክፍለዘመን ማሳያ ሲሉ የገለጹትን የዚህን ስምምነት የአፈጻጸም ሂደትም አድንቀዋል፡፡

ይሁንና የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ድረስ በትግራይ ክልል እንዳሉ በመጥቀስ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ፤ "በሕዳር ወር ስምምነት ከተደረሰ በኋላ አስፈላጊና ቁርጠኝነትን በሚጠይቁ ተግባራት ዙሪያ ከፍተኛ መሻሻሎች አሉ፡፡ በተለይ ተኩሶች ቆመዋል፤ ሰብዓዊ ድጋፍ እየገባ ነው፤ አገልግሎቶች እየተመለሱ ነው፣ ሕወሓት የከባድ መሳሪያ ትጥቆቹን መፍታቱን ተመልክተናል፡፡ በተጨማሪም ኤርትራን ጨምሮ የውጭ ኃይሎች ከትግራይ ክልል እየወጡ ነው፡፡ ይሄ አልተጠናቀቀም፤ በሂደት የሚሆን ነው፡፡ ነገር ግን በሰላም ስምምነቱ የተካተቱና ቃል የተገቡ ተግባራትን ከመፈጸም አኳያ በትክክለኛው አቅጣጫ እየሄዱ ያሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየተመለከትን ነው፡፡" ብለዋል።

ለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም እንዲሁም እርቅን እና ተጠያቂነትን ላማከለ የሽግግር ፍትህ ሂደት ዩናይትድ ስቴትስ የምታደርገውን ድጋፍ በተመለከተ ከጠቅለይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከሕወሓት ተደራዳሪ ቡድኖች ጋርም መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ግጭት ጋር በተያያዘ፣ ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገራት የተለያዩ ምርቶቻቸውን ለዩናይትድ ስቴትስ ገበያ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ወደሚፈቅደው የአጎአ ተጠቃሚነት መመለስ የምትችለው በሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም በምታሳየው መሻሻል መሰረት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

"እንደምታውቁት ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን ከአጎአ ፕሮግራም ካለፈው ዓመት 2022 ጥር ወር ጀምሮ አግዳለች፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጥሰት ከመፈጸም ጋር በተያያዘ በህጉ መሰረት የተወሰነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ተጠቃሚነቱ ለመመለስ የተቀመጡላት ግልጽ የሆኑ መለኪያዎች አሏት። እነዛ ግቦች እንዲሳኩ ከመንግስት ጋር መስራታችንን እንቀጥላለን፡፡ በተለይ የግጭት ማቆም ስምምነቱን መተግበር ለዚህ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እኔ ተስፋ እማደርገውና እምጠብቀውም ይህ እንደሚቀጥል ነው፡፡ ለመረጃ ያህል የአጎአ ፕሮግራም የሚመራው በዩኤስ የንግድ ክፍል ነው፡፡ እነሱ የአጎአ ተጠቃሚነትን የብቃት መስፈርቶች የሚያጣሩበት አመታዊ ግምገማ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አጎአ ለመመለስ ያላትም ፍላጎት እንረዳለን፡፡ እናም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተፈጻሚ ባደረገች መጠን፣ ለመመለስ ትክክለኛውን መንገድ እየተጓዘች ነው፡፡"

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ በኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው እና ችግሩ በውይይት መፈታት እንዳለበትም መግለጻቸውን መስሪያ ቤታቸው ያወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡ ሚኒስትሩ ነገ መጋቢት 7 ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ተወያይተው ወደ ኒጀር እንደሚያመሩ ይጠበቃል፡፡

XS
SM
MD
LG