በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንክን ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የፊታችን ረቡዕ፤ መጋቢት 6 ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱ የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ዛሬ አስታወቁ።

ብሊንከን ኢትዮጵያ የሚሄዱት ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭት ማስወገጃውን ሥምምነት አተገባበር ለመከታተል፣ ሰላምን ለማጠናከርና በሽግግሩ ወቅት ፍትህ እንዲገኝ የሚደረገውን ጥረት ለማበረታታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመምከር መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ወቅት የሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮችንና የሲቪል ማኅበራት ተጠሪዎችን እንደሚያነጋግሩና ሰብዓዊ እርዳታ በሚቀላጠፍበት፣ በምግብ ዋስትናና በሰብዓዊ መብቶች ላይ እንደሚመክሩ ታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንክን በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ተገናኝተው በዓለም አቀፍ እና በአህጉራዊ ደረጃ ቅድሚያ ትኩረት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ። ዋሽንግተን ውስጥ በተካሄደው የዩ ኤስ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ በተገቡት ቃሎች ዙሪያ ይነጋገራሉ።

አፍሪካ በዓለም አቀፍ ተቋማት በቋሚ መቀመጫ እንድትወከል ዩናይትድ ስቴትስ የምትደግፍ መሆኗን እንደሚያረጋግጡ ከቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ቢሮ የወጣው መግለጫ አውስቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ ጉብኝታቸው በኋላ በማግስቱ ሀሙስ የመጀመሪያቸው ለሚሆነው ጉብኝት ወደኒጀር እንደሚያቀኑ መግለጫው አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG