በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለስደተኛ ልጆችና ቤተሰቦች የተለዩ ማዕከሎች እየመሰረቱ መሆናቸው ታወቀ


ዶርትመንድ በሚባል የጀርመን ከተማ በባቡር የገቡ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ምግብ በሚሰጥበት አዳራሽ [አሶሽዬትድ ፕረስ (AP)]
ዶርትመንድ በሚባል የጀርመን ከተማ በባቡር የገቡ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ምግብ በሚሰጥበት አዳራሽ [አሶሽዬትድ ፕረስ (AP)]

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች አገልግሎትና የልጆች መርጃ ድርጅት ከጦርነትና ከክትትል ሸሽተው የሚሰደዱትን ልጆች ቤተሰቦችን ለመርዳት 20 ማእከሎችን እየመሰረቱ ነው።

ልጆችና ቤተሰቦች ግሪስ እንደገቡ ማሴዶንያን፣ ሰርቢያን ክሮሽያንና ስሎቬንያን በሚያካትተው የባልካን የስደት መስመር በሚጓዙበት ወቅት ብዙ አደጋ ስለሚገጥማቸው በሚመሰረቱት ማዕከሎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ነው የታቀደው።

ማዕከሎቹ ልጆች የሚጫወቱባቸው ቦታዎች አሏቸው። ቤተሰቦቻቸው ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶች፣ የጸጥታ ደህንነትና ምክር የሚያገኙባቸው ማዕከሎች ይሆናሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች አገልግሎት ረዳት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ፣ ስደተኛ ቤተሰቦች በተለይም ልጆች ለብዙ ችግር የተጋለጡ ናቸው ብለዋል። ብዙዎቹ ልጆች ብቻቸውን ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ይነጠላሉ። ልጆቹ ታድያ ይታመማሉ፣ ለስቃይ፣ ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ለግጭትና ለወሲብ አገልግሎት አደጋ ይጋለጣሉ ሲሉ ቮልከር ተርክ አስገንዝበዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ወደ ግሪስና ማሴዶንያ ድንበር ተጉዘው ባስተዋሉት መሰረት በሰደተኛ ልጆች ላይ የሚንጸባረቀውን የፍርሀት ስሜት እንደተገነዘቡ ምክትል ከፈተኝ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

“ልጆች ብቻቸውን በብርድና በጨለማ ሲንከራተቱ ታያለህ። እነዚህ ልጆች ቤተሰቦቻቸው ጉዞ ላይ የጠፉባቸው ናቸው። አውቶብሶች ላይ ሲጭኗቸው ከቤተሰብ ጋር የመለያየት ሁኔታ ይፈጠራል። በጨላማ በማያውቁት ቦታ ላይ ሲንከራተቱ ይጨነቃሉ።” ብለዋል።

የስደተኞቹ ማዕከሎች መጀመርያዎቹ መስራት የጀመሩት ከሁለት ሳምንታት በፊት ሲሆን በየዕለቱ 40 እና 50 የሚሆኑት ጠፍተውባቸው ከነበሩት ወላጆቻቸው ጋር እየተገናኙ ነው። ሀያዎቹ መጠልያ ሰፈሮች በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ አገልግሎት ላይ ይውላሉ ብለዋል ቮልከር ተርክ።

በአሁኑ ወቅት በቱርክ በኩል በባህር ወደ ግሪስ ከሚሰደዱት ሰዎች መካከል ወደ 60 ከመቶ የሚጠጉት ሴቶችና ልጆች እንደሆኑ ባለፈው መስከረም ወር ግን ሴቶችና ልጆች 27 ከመቶ እንደነበሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች አገልግሎት ጠቁሟል። የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ዘጋቢ ሊዛ ሽላይን ከጄኔቫ የላከችውን ዘገባ አዳነች ፍሰሀየ ታቀርበዋለች።

ለስደተኛ ልጆችና ቤተሰቦች የተለዩ ማዕከሎች እየመሰረቱ መሆናቸው ታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:27 0:00

XS
SM
MD
LG