በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከኤርትራ የተሰደደ ኤርትራዊ በሚላን ከተማ ስደተኞችን ይረዳል


በዚህ ሳምንትየጀኔቫ ሚኒስተሮች፣ የክልል አስተዳዳሪዎች እና ከፍተኛ ሃላፊዎች በአውሮፓ በብዛት የሚያልፉት ስደተኞችና ፍልሰተኞች እንዴት ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ እንደሚሸጋገሩ ለመወያየት እየተዘጋጁ ይገኛሉ። ሪኪ ሽርዮክ (Ricci Shryock) በሚላን የከተማዋ ዋና የስደተኞችና ፍልሰተኞች መሸጋገርያ ጣብያ የሚሰራ አንድ ኤርትራዊ ወጣት አነጋግራ የላከችው ዝርዝር።

የጣልያን ሚላን ከተማ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከኤርትራ ወደ አውሮፓ በመርከብ ተሻግረው የሚመጡ ስደተኞችና ፍልሰተኞች ቀዳሚ ማረፍያ ናት።

ስደተኞች ወደ ከተማዋ ሲገቡ ግን፣ የት እንደሚሰፍሩ ወይም ከይትኛው ቦታ ተሻግረው ወደ ሌላ ቦታ እንደሚሄዱ፣ ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ስለመጪው እድላቸው ውሳኔ ላይ መድረስ፣ ሰባት ቀናት ብቻ ነው የሚሰጣቸው።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ፣ በዚህ ሳምንት የጀኔቫ ሚኒስተሮች፣ የክልል አስተዳዳሪዎች እና ከፍተኛ ሃላፊዎች በብዛት ወደ አውሮፓ እየገቡ ያሉት ስደተኞችና ፍልሰተኞች እንዴት ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ እንደሚሸጋገሩ ለመወያየት እየተዘጋጁ ነው።

ከማንኛውም ሃገር በላይ በመርከብ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ብዙዎች ስደተኞች ኤርትራውያኖች መሆናቸው ታውቋል። የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ከ 35,000 በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ከኤርትራ ወደ ጣልያን በዚህ ዓመት በቻ በመርከብ እንደገቡ አስታውቋል።

ጽገሃንስ ወልደስላሴ ከኤርትራ እአአ በ 2007 ነው አገሪቷን ለቆ የተሰደደው። አሁን ሚላን በሚገኘው የከተማዋ ዋና የስደተኞችና ፍልሰተኞች መሸጋገርያ ጣብያ ስደተኞችን በመርዳት ሥራ ላይ ተሰማርቷል።

እኔም እንደባርያ ከሁለት እስከ ሶስት ለሚሆን ጊዜ በነጻ ሰርቻለው። በመጨረሻ ባርያ አልሆንም ብዬ ተሰደድኩ።
ጽገሃንስ ወልደስላሴ (በሚላን ከተማ ስደተኞች መሸጋገርያ ጣብያ የሚሰራ ኤርትራዊ)

ይህ አቶ ጽገሃንስ እና፥ የአሜሪካ ድምፅ ጋዜጠኛ ሪኪ ሽርዮክ (Ricci Shryock)ስለዚህ ሁኔታ ያካሄዱት ቃለ ምልልስ ነው።

ጽገሃንስ ወልደስላሴ፡ ሚላን በኤርትራውያን ስደተኞች በጣም የታወቀ ቦታ ነው። ወጣቶች በብዛት ከኤርትራ ወደዚህ ይመጣሉ። በየቀኑ ከ200 በላይ የሚሆኑ ህፃናት፡ ጨቅላ ልጆች፣ ነፍሰጦሮች በረሃና ባህር ተሻግረው ወደዚህ ሲመጡ በጣም ያሳዝናል። በተለይ ከዚች ከትንሽ ሃገር ይሄንን የሚያክል ስደተኞች ሲመጡ ከሃገሪትዋ ማንም እንደማይቀር ያሳያል። ሰዎች ተስፋ ስለቆረጡ ነው ሃገሪትዋን ለቀው የሚወጡት። ለውጥ መጠበቅ ሰልችቷቸዋል። ሁሉንም ነገር ነው ትተው፣ የሚመጡት።

ሪኪ ሽርዮክ፡ እዚህ ሚላን ከገቡ በውኃላ ምን አይነት ሁኔታ ነው የሚጠብቃቸው?

ጽገሃንስ ወልደስላሴ፡ በሚላን ከተማ ሰው እንደ ሰው አይቆጠርም። ይህ ደግሞ በዚህ ከተማ ውስጥ ብቻ ያለ ችግር ሳይሆን፣ በሌሎች ቦታዎችም የሚታይ ነው። መጀመርያ ሲመጡ አይመዘግቧቸውም። ከዛም በኃላ በጣም ለትንሽ ጊዜ ከሰባት እስከ ስምንት ለሚሆኑ ቀናት በቻ ነው እርዳታ የሚሰጣቸው። ከዛም ወደሚፈልጉበት ቦታ ለመሄድ የመጓዣ ገንዘብ መጠየቅ አለባቸው። ከስምንት ቀናት በላይ ከቆዩ ግን፣ በጣልያን የፓለቲካዊ ጥገኝነት መጠየቅ አለባቸው። ስለዚህ በጥድፊያ ነው ይህንን ሁሉ መጨረስ ያለባቸው። አንዳንዴም የመረጃ እጦት ሊኖር ይችላል። ምክንያቱም የት እንደሚሄዱ፣ ገንዘብ ከዬት እንደሚመጣ ላያውቁ ስለሚችሉ። አንዳዴም ገንዘብ ወላጆቻቸው እንዲልኩላቸው ስለሚፈልጉ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። መንቀሳሻ ሰነዶች ለማግኘት ፣ መጓጓዣ ትኬት ለመቁረጥ የሚተባበር ሰው ያስፈልጋቸዋል። ይህንን ሁሉ ጉዳይ በሰባት ቀናት ጨርሶ ወደ ሌሎች ሃገሮች መሻገር በጣም ከባድ ነገር ነው።

በጣልያን የሚተገኘው ሚላን ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ብዙ ከኤርትራ ወደ አውሮፓ በመርከብ ተሻግረው የሚመጡ ስደተኞችና ፍልሰተኞች ቀዳሚ ማረፍያ ከተማ ነች

ሪኪ ሽርዮክ፡ ሰዎችን ስታነጋግር ዋና ለመሰደድ የሚያበቃቸው ምክንያት ምንድን ነው ብለው ይነግሩሃል?

ጽገሃንስ ወልደስላሴ፡ ብዙ ሰዎች የሚነግሩኝ ዋና ምክንያት በኤርትራ ያለውን በውትድርና መሰለፍ፣ የኑሮ ውድነትና በሃገሪቷ ያሉ ችግሮች መቋቋም እንዳቃታቸው ነው የሚገልጹት።

ሪኪ ሽርዮክ፡ በውትድርና መሰለፍ ስትል ምን ማለትህ ነው?

ጽገሃንስ ወልደስላሴ፡ እንድያውም ውትድርና መባሉ ሁኔታውን በግልጽ አያስረዳም። ምክንያቱም ውትድርና በሁሉም ሃገር ያለ ነው። እነዚህ ሰዎች ግን ወታደሮች አይደሉም። እንደ ባርያ ነው የሚቆጠሩት። ምርጫ በሌለበት፥ የስራ ገደብ በሌለበት ሁኔታ ይሰራሉ። እንዲሁም በስልጠና እንዲሳተፉ ይገደዳሉ። ውትድርና እንለዋለን ግን ልክ አይደለም። ክፍያ የሌለበት ስራ በውትድርና መልክ ባርነት ነው።

ሪኪ ሽርዮክ፡ መቼ ነው ከኤርትራ የወጣኅው?

ጽገሃንስ ወልደስላሴ፡ እአአ በ 2007 ነው አገሬን ለቅቄ የወጣሁት። ወደ ስምንት ዓመት ሆኖኛል። እኔም እንደባርያ ከሁለት እስከ ሶስት ለሚሆን ጊዜ በነጻ ሰርቻለው። በመጨረሻ ባርያ አልሆንም ብዬ ተሰደድኩ።

የሃገሪቱ መሪዎች የጽገሃንስ ወልደስላሴን እና የሌሎችን የስደተኞች ክሶች ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ነው በተደጋጋሚ የሚገልጹት።

ይህንን ቃለ ምልልስ ሪኪ ሽርዮክ (Ricci Shryock)በሚላን የከተማዋ ዋና የስደተኞችና ፍልሰተኞች መሸጋገርያ ጣብያ ከሚሰራ አንድ ኤርትራዊ ወጣትን አነጋግራ ነው የላከችው። ሙሉውን ዝርዝር ሳሌም ሰለሞን አቅርባዋለች። ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ከኤርትራ የተሰደደ ኤርትራዊ በሚላን ከተማ ስደተኞችን ይረዳል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:03 0:00

XS
SM
MD
LG