የፓልሚራን ከተማ ከእስላማዊው ጽንፈኛ አይሲስ እጅ አውጥቶ መልሶ የተቆጣጠረበትን ድል፤ በቡድኑ ላይ ለሚያካሂደው ቀጣይና መጠነ-ሠፊ ዘመቻ የማቀናበባበሪያ መነሻ ጭምር ሊያደርገው ማቀዱን የሶሪያ ጦር ሠራዊት አስታወቀ።
የአገሪቱ ጥንታዊ ቅርሶች ጥበቃ ተቋም ተጠሪ በበኩላቸው፤ “ከቡድኑ የከፋ የጥቃት የተረፈው ይህ ታሪካዊ ሥፍራ ሌላ ይበልጥ አስፈላጊና የላቀ ጠቀሜታም አለው፤” ይላሉ። የሶሪያ መንግስት ኃይሎች በሩሲያ የዓየር ድብደባ እየታገዙ፤ ከሁለት ሺህ ዓመታት እድሜ በላይ ባስቆጠሩ ሃውልቶች ላይ ያደረሰውን እጅግ የከፋ ውድመት ጨምሮ ጽንፈኛው ቡድን በጥንታዊቱ የፓልሚራ ከተማ አስፍኖት ለነበረውና ለአሥር ወራት ለዘለቀው ቁጥጥር ማብቂያ አበጅተዋል።
ዋና መቀመጫውን በብሪታንያ ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ቡድን ይፋ እንዳደረገው፤ ፓሊሚራ’ን ከቡድኑ እጅ ለማስለቀቅ በተካሄደው ውጊያ ቁጥራቸው ከአራት መቶ በላይ የሚደርስ የሸማቂው ቡድን ተዋጊዎችና ሌሎች ቁጥራቸው ከ180 በላይ የሚደርስ የመንግስቱ ኃይሎች ተዋጊዎች ተገድለዋል።