በሦሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቅበት ባሁኑ ወቅት፥ የሩሲያ ጦር አውሮፕላኖች ”ክሬምሊን - ያሸባሪ ድርጅቶች” ሲል የጠራቸውን የሽምቅ ተዋጊዎች ጠንካራ ይዞታዎች በቦንብ መደብደባቸውን ቀጥለዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን የሸመገሉት ሩሲያና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ ሩሲያ፥ በሦሪያ የሚገኙ የእስላማዊ መንግሥቱንና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለውን የአል ኑሥራ ግንባር አሸባሪ ቡድኖች በቦምብ የመደብደብ ዘመቻዋን የመቀጠል እቅድ አላት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ፥ በሦሪያ የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሃገሪቱ አቆጣጠር ተግባራዊ እንደሚሆን እየተጠበቀ ባለበት ሁኔታ ሲናገሩ፥ የሦሪያና ኢራቅን ጦርነት ማብቃት፥ የእስላማዊ መንግሥት ነኝ በሚለው የአሸባሪዎች መረብ ላይ ድል ለመጎናጸፍ የሚያስችል ዓይነተኛ መሣሪያ ነው ብለዋል።
ፕሬዘዳንት ኦባማ ከመንግሥታቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው፥ የተኩስ አቁሙ፥ በሦሪያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ሁኔታን የመፍጠር አቅም ይኖረዋል ሲሉ በተጨማሪ አስረድተዋል።
”ተቀናቃኝ ወገኖች ተኩስ ለማቆም የደረሱበት ውሳኔ፥ ሰላማዊ ድርድሩን በሃቀኝነት ያካሂዱ እንደሁ የሚፈተሹበት ይሆናል። ከዚህ ቀደም ቪዬና ላይ የተደረሰው ስምምነት ግልፅ ነው። ይበልጥ ሁሉንም ወገን አሳታፊ የሚሆን፥ በሕዝብ የተወከለ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል የሽግግር ሂደት ነው። ነፃ ምርጫ ማካሄድን ተከትሎ አዲስ ሕገ መንግሥት ይረቀቃል። በድጋሚ እናገራለሁ፥ ይህ እኔ ያዋጣል ብዬ ያመንኩበት የሦሪያ መጻዒ ሁኔታን የተመለከተው የሽግግር ሂደት ባሻር አል-አሳድን አይጠቀልልም።” ብለዋል ፕሬዘዳንት ኦባማ።
የሚጠበቀው የተኩስ አቁም፥ በሃገሪቱ የፖለቲካ ሽግግርና መረጋጋት ሊያመጣ ይችላል፥ የእስላማዊ መንግሥት ነኝ ባዩን የአሸባሪ ቡድን ስጋት ይቀንሳል ተብሎ በዩናይትድ ስቴትስና በዓለምአቀፍ የሦሪያ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖች ይታገዛል።