ውሳኔ-ሕዝቡ፣ ግዛቱ አምስቱን የአካባቢው ክልሎች ይዞ እንዳለ ይቆይ እንደሆን ወይም ወደ አንድ ግዛት ተጠቃለው በከፊል የራስ ገዝ-አስተደር ስር ይሆኑም እንደሆን የሚለይበት እንደሚሆን ታውቋል።
በዳርፉር የርስ በርስ ግጭት ምክኒያት፣ ወደ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ ዛሬም ከቤት ንብረቱ እንደተፈናቀለ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ውጩ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ዳርፉር ውስጥ ያለው ያልተረጋጋ ሁኔታና በርካታ ሕዝብ ከቤቱ ተፈናቅሎ ያለ በመሆኑ፣ ውሳኔ-ሕዝቡ የተሟላ ካለመሆኑም በላይ፣ ተዓማኒነትም አይኖረውም ሲል ስጋቱን አመልክቷል።
የሱዳኑ የማስታወቂያ ሚኒስትር አህመድ ቢላል ግና፣ ውሳኔ-ሕዝቡ የሚካሄደው፣ ዳርፉር ከመቼውም ጊዜ በላይ የሰከነና የተረጋጋ ሰላም ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው ብለዋል። "ሱዳንም" አሉ ሚኒስትሩ በመቀጠል፣ "እ.አ.አ. በ2011 ዓ.ም. በሱዳን መንግሥትና በሽምቅ ተዋጊዎቹ የነፃነትና የፍትህ ንቅናቄ መካከል ዶሃ ላይ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እያደረገች መሆኗ ሊጤን ይገባዋል።"ብለዋል።
"ይህ ደግሞ፣ ማንም እንደሚያውቀው፤ የዶሃን ስምምነት በተመለከተ መንግሥቴ የገባው የፖለቲካ ቃል-ኪዳን ስለሆነ፣ ይህን የሦስት ቀን ውሳኔ-ሕዝብ ተግባራዊ ማድረጉን ይገፋበታል" ሲሉም አክለዋል የሱዳኑ ማስታወቂያ ሚኒስትር።
አንዳንዶቹ የዶሃ ስምምነት፣ በጠላትነት ያለመተያየትን ጨምሮ ዘላቂ የተኩስ አቁም ውል ማድረግን፣ የሲቪል ማኅበረሰብና ቡድኖችን ነፃነትና የሰብዓዊ መብት ጥበቃን፣ ዳርፉር ውስጥ የአስተደርና የሥልጣንና የሀብት ክፍፍልን ይጨምራል።
በሰላሙ ስምምነት መሠረትም፣ ዘላቂው የዳርፉር አስተዳደራዊ ሥልጣን፣ በውሳኔ-ሕዝቡ እንደሚደነገግ ተመልክቷል።
ጄምስ ባቲ ያጠናቀረውን ዘገባ አዲሱ አበበ አቅርቦታል ከዚህ በታች ካለው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።