በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳኑ ፕሬዝደንት ለቀረበባቸው የዘር ማጥፋት ክስ ምላሽ እንዲሰጡ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች


የሱዳኑ ፕሬዚደንት አል-በሽር ወደ ቻድ ሲያመሩ
የሱዳኑ ፕሬዚደንት አል-በሽር ወደ ቻድ ሲያመሩ

የቻድ የአገር ውስጥ ሚኒስትር አል-በሽር እንደማይታሰሩ ማረጋገጫ ሰጥተዋል

የቻድ መንግስት የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ወይንም ICC አባል አገር በመሆን የተፈረመውን ስምምነት ባለማክበር ኦማር አልበሽርን ባለማሰሩ የዩናይትድ ስቴይትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያወጣው ወቀሳ ወይንም መቆላጨት የለም።

ነገር ግን በሱዳን ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲሰፍን ፕሬዝደንት አልበሽርም ሆኑ ሌሎች ክስ የተመሰረተባቸው ባለስልጣናት ለICC ምላሽ መስጠት አለባቸው ትላለች ዩናይትድ ስቴይትስ።

ዛሬ ፕሬዝደንት አልበሽር ክስ ከተመሰረተባቸው ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የICC ስምምነትን ከፈረሙ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችውን ቻድን ጎብኝተዋል። በዳርፉር ግዛት ለሰባት አመታት ያህል በዘለቀው ጦርነት ኢሰብአዊ ወንጀል ፈፅመዋል ሲል ፕሬዝደንቱን ጨምሮ ሌሎች ወታደራዊ መሪዎችን በወንጀል ከሶ ICC፤ በተገኙበት እንዲታሰሩ ማደኛ አውጥቶባቸዋል።

ባለፈው ሳምንት በጦር ወንጀለኝነት ከወጣው ክስ በተጨማሪ በሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤት በአል-በሽር ላይ የዘር ማጥፋት ክስ ጨምሮባቸዋል። የዳርፉር ግጭት 300 ሽህ ሰዎችን ሲገድል ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሌሎችን ደግሞ ማፈናቀሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይተምናል። ስደተኞቹ ብዙውን ጊዜ ወደ ጎረቤት ቻድ ያመራሉ። የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ለአመታት የሻከረ ሲሆን አንደኛው መንግስት ሌላኛውን “ወታደሮች ያሰለጥናል፣ በእጅ አዙር ይወጋኛል” በማለት እርስ-በርስ መወነጃጀልም ይታያል።

በእንጃሚና ንግግር ያደረጉት አል-በሽር የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ተሻሽሏል ብለዋል። የቻድ የአገር ውስጥ ሚኒስትርም አል-በሽር እንደማይታሰሩ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ዛሬ በዋሽንግተን የጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል-አቀባይ ፒ.ጄ ክራውሊ ቻድ ለምን የፈረመችውን የICC ግዴታ አልተወጣችም ሲሉ ጠይቀዋል። የሱዳኑ መሪ በስተመጨረሻ ለፍርድ እንደሚቀርቡም ክራውሊ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG