በምዕራብ ሐረርጌ መቻራ፣ በወለጋ ነቀምትና በሊበን ነጌሌ ከተሞች ውስጥ የተለያዩ የተቃውሞና የግጭት እንቅስቃሴዎች ትናንትናና ዛሬ እንደነበሩ የየአካባቢው ነዋሪዎች ለአፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍላችን ባልደረባ ለቱጁቤ ኩሣ ገልፀዋል፡፡
በምዕራብ ሐረርጌ መቻራ ከተማ ትናንት ሰልፍ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን ሰልፉን ለመበተን የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰዳቸውንና በሕይወትና በአካል ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩን የሚናገሩ ጥቆማዎች ደርሰውናል፡፡
የከተማዪቱን ባለሥልጣናት ለማግፕት ያደረግነው ጥረት አልተሣካም፡፡
ወለጋ ነቀምት ውስጥም የፀጥታ ኃይሎች ከቤት ቤት እየዞሩ ሰው መያዛቸውንና ድብደባ ሲያካሂዱ እንደነበር አንድ የነቀምት ከተማ ነዋሪ ቱጁቤ ነግረዋታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን አምቦ ከተማ ውስጥ በማረሚያ ቤቱ በደረሰ ቃጠሎ ስድስት እሥረኞች መሞታቸውንና አስከሬኖቻቸው ለቤተሰቦቻቸው መሰጠታቸውን አንድ የከተማዪቱ ነዋሪ ነኝ ያሉ ሰው ለጃለኔ ገመዳ ቢናገሩም የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ግን የጠፋ ሕይወትም፣ ያመለጠ እሥረኛም የለም ሲሉ ለአንድ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታተመ ለሚወጣ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ነገሌ ከተማ ውስጥ በተደረገ ሰልፍ “ሻኪሶ ውስጥ የህዝብ ኃብት እየተዘረፈ ነው፤ ዘረፋው ይቁም” ሲሉ ተቃውሞ ማሰማታቸውን አንድ የአፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍል ባልደረባ ሶራ ሃለኬ ያነጋገራቸው ነዋሪ ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ የተካሄደ ሰልፍም፣ የተደበደበም ሆነ የታሠረ ሰው የለም ብለዋል የሊበን ወረዳ ምክትል ሳጅን ሚካኤል።
በሁሉም አካባቢዎች “የታሠሩት ይፈቱ፤ ስለተገደሉት ካሣ ይከፈል፤ የደረሰውን ጉዳት አጣሪ ኮሚሺን ተቋቁሞ ይመርምር፤ ወታደሮች አይደብድቡን፤ አያሰቃዩን፤ ወታደሮች ከከተሞች ይውጡ” የሚሉ ጥያቄዎች ይሰሙ እንደነበር ታውቋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።