በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአገሪቱ ጦር በታጣቂዎች የተያዙ ሁለት የዐማራ ክልል ከተሞችን እንዳስለቀቀ ነዋሪዎች ገለጹ


ፎቶ ፋይል፦ ላሊበላ ከተማ በጭርፍታ የሚያሳይ ምስል
ፎቶ ፋይል፦ ላሊበላ ከተማ በጭርፍታ የሚያሳይ ምስል

የዐማራ ክልል የአካባቢ ታጣቂዎች፣ ከያዟቸው ሁለት ዋና ዋና ከተሞች፣ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ተገፍተው እንደወጡ፣ ነዋሪዎች፣ ዛሬ ረቡዕ አስታወቁ።

በክልሉ፣ በመከላከያ ሠራዊቱ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል፣ ባለፈው ሳምንት፣ የተኩስ ልውውጥ ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ የጦር ሠራዊቱ፣ ታጣቂዎቹን ከከተሞቹ ገፍቶ ሲያስወጣ፣ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት፣ በዐማራ ክልል ሁለተኛው ትልቁ ከተማ የኾነውን ጎንደርን፣ ትላንት ማክሰኞ ሲቆጣጠር፣ ዛሬ ረቡዕም ወደ ላሊበላ ከተማ ገብቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ፣ ግጭቱ ወደተካሔደባቸው የክልሉ ዋና መዲና ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ያቋረጠውን በረራ፣ ነገ ኀሙስ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የዐማራ ክልል ግጭት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት፣ በሰላም ስምምነት ካበቃበት ጥቅምት ወር ወዲህ የተከሠተ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እንደኾነ ተገልጿል፡፡ በግጭቱ፣ የአገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት በትጥቅ የተገዳደሩት የፋኖ ታጣቂዎች፣ ላሊበላንና የጎንደር ከተማን በከፊል ይዘው ቆይተዋል፡፡

የሙሉ ጊዜ ተዋጊ ያልኾነው የፋኖ ታጣቂ፣ በችግር ጊዜ በጎ ፈቃደኛ ተዋጊ፣ በሰላም ጊዜ ደግሞ ሰላማዊ ሕይወትን በሚመሩ የዐማራ ክልል ነዋሪዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አጋር ነበር። ኾኖም፣ የፌዴራል መንግሥት፣ የክልሉ ልዩ ኀይል ወደ ጸጥታ ተቋማት ለማዋሐድ በዘረጋው ፕሮግራም አፈጻጸም፣ የዐማራን መከላከያ ለማዳከም እየሞከረ ነው፤ በሚል ውንጀላ ምክንያት ግንኙነታቸው ሻክሮ ወደ ግጭት አምርቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ውንጀላውን አይቀበልም።

ትጥቃዊ ግጭቱ እያደር መባባሱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ በዐማራ ክልል እስከ ስድስት ወራት ሊቆይ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዐውጇል፡፡ የመንግሥት ቃል አቀባይም ኾነ መከላከያ ሠራዊቱ፣ ስለ ኹኔታው፣ ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

ሮይተርስ ያነጋገረው፣ አንድ የጎንደር ነዋሪ የኾነ የፋኖ ታጣቂ፣ በአድማ በታኝ ፖሊሶች እና ለመንግሥት ታማኝ በኾኑ የፀረ ሽምቅ ታጣቂዎች የተደገፈው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ትላንት ማክሰኞ፣ የፋኖ ተዋጊዎችን ከከተማው ገፍቶ እንዳስወጣቸው ገልጿል።

ከፍተኛ ውጊያ ነበር። መከላከያ ሠራዊቱ ታንክን ተጠቅሟል። የእኛ ተዋጊዎች ደግሞ፣ ክላሺንኮቭ ብቻ ነው የነበራቸው፤”

ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ይኸው የፋኖ ታጣቂ፣ “ከፍተኛ ውጊያ ነበር። መከላከያ ሠራዊቱ ታንክን ተጠቅሟል። የእኛ ተዋጊዎች ደግሞ፣ ክላሺንኮቭ ብቻ ነው የነበራቸው፤” ሲል፣ በትጥቅ የተወሰደባቸውን የኀይል ብልጫ አስረድቷል።

አንድ የጎንደር ከተማ ባለሥልጣን፣ የፋኖ ታጣቂዎች፣ ከተማዪቱን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረው እንደነበር ሲገልጹ፣ ሌላው የጎንደር ነዋሪ በበኩሉ፣ ትላንት ማክሰኞ ከቀትር በኋላ፣ መከላከያ ሠራዊት ወደ መሀል ከተማዋ ሲገባ ማየቱን ተናግሯል።

ሁለት የላሊበላ ነዋሪዎች ለሮይተርስ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ የገባው፣ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ነው፡፡ ትላንት፣ ከከተማዋ ወጣ ባሉ አካባቢዎች፣ ከፍተኛ ውጊያ ተካሒዶ እንደነበር፣ ነዋሪዎቹ አውስተዋል። ሁለት የባሕር ዳር ነዋሪዎች ደግሞ፣ ከቀናት ውጊያ በኋላ ዛሬ ረቡዕ፣ ከተማዪቱ እንደተረጋጋች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ያነጋገረውና አያሌው ሲል ስሙን ያስተዋወቀ ሌላው የላሊበላ ከተማ ነዋሪ፣ የኢትዮጵያ ጦር፣ በከተማዋ ሹምሽሃ አየር ማረፊያ ላይ እንደሰፈረ ተናግሯል። “ፋኖ፣ ከተማዋን እየተወ በመውጣት ወደ ጫካ ገብቷል፤” በማለት፣ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ፣ ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ገልጿል።

በዐማራ ክልል የጋዜጠኞች ስምሪት እንደተከለከለ የጠቀሰው አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ በአካባቢው ያለውን ኹኔታ፣ በገለልተኛነት ለማጣራት እንዳልቻለ አመልክቷል።

የዐማራ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር፣ ትላንት ማክሰኞ ማምሻውን፣ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ጎንደር ከተማ እና የክልሉ ርእሰ መዲና ባሕር ዳር፣ ከፋኖ ይዞታ “ነፃ” እንደወጡ ቢገልጽም፣ ዛሬ ረቡዕ መግለጫውን አንሥቶታል። የአስተዳደሩ ቃል አቀባይም፣ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም።

በዐማራ ክልል በተካሔደው የፋኖ ታጣቂ እና የመከላከያ ሠራዊቱ ውጊያ፣ በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት፣ እስከ አሁን ከክልሉ የወጣ ኹነኛ መረጃ አልታየም፡፡ የላሊበላ ነዋሪዎች ግን፣ ከተዋጊዎቹ አባላት በደርዘን የሚቆጠሩ እንደተገደሉ፣ ትላንት ማክሰኞ ለሮይተርስ ገልጸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG