· ችግሩ በውይይት እና በድርድር የሚፈታበት መንገድ ዝግ አይደለም- መንግሥት
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የዐማራ ክልል ዋና ከተማ ወደኾነው ባሕር ዳር ከተማ የሚያደርገውን በረራ እንደሰረዘ፣ ዛሬ ማክሰኞ አስታወቀ።
ባለፈው ሳምንት፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በፌዴራል ወታደሮች መካከል ግጭት በመቀስቀሱ፣ ብሔራዊው አየር መንገድ፣ ወደ ክልሉ ሦስት የአውሮፕላን ማረፊያዎች የሚያደርጋቸውን በረራዎች ሲሰርዝ፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ፣ በክልሉ ወደሚገኝ የትኛውም የአየር ማረፊያ እንደማይበር ገልጿል።
አየር መንገዱ በመግለጫ እንዳሰፈረው፥ “ረቡዕ፣ ኀሙስ እና ዐርብ፣ ወደ ደሴ (ኮምቦልቻ)፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና ባሕር ዳር ሊደረጉ የነበሩ በረራዎች ተሰርዘዋል፤” ብሏል።
በዐማራ ክልል የተስፋፋው ግጭት፣ ባለፈው ሳምንት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፣ እስከ ስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲያወጣ ምክንያት ኾኗል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በበኩሉ፣ ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ በዐማራ ክልል ያለው ችግር፣ በውይይት እና በድርድር የሚፈታበት መንገድ አሁንም ዝግ እንዳልኾነ አስታውቋል።
ረቡዕ፣ ኀሙስ እና ዐርብ፣ ወደ ደሴ (ኮምቦልቻ)፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና ባሕር ዳር ሊደረጉ የነበሩ በረራዎች ተሰርዘዋል፤”
በመንግሥት የብዙኀን መገናኛ የቀረበው የተቋሙ መግለጫ፣ በዐማራ ክልል፣ “ለዘረፋ የተደራጁ ጥቂት ኃይሎች” አሁን ላይ፣ “መንግሥታዊ መዋቅሮች እንዲፈርሱ፣ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት እንዲያቋርጡ፣ አንዳንድ ከፌዴራል መንግሥት ጋራ የሚያገናኙ የመንገድ መሠረት ልማቶች እንዲዘጉ በማድረግ፣ ሕዝቡ ላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ፤” በማለት ወንጅሏል።
“በማወቅም ይኹን ባለማወቅ፣ በሕገ ወጡ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ” በማለት የገለጻቸውን ግለሰቦች እና ቡድኖች፣ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ይህም ኾኖ ችግሩ፣ በውይይት እና በድርድር የሚፈታበት መንገድ፣ አሁንም ዝግ እንዳልኾነ፣ የደኅንነት ተቋሙ ሲጠቁም፣ ለዚኽም ተከታታይ ጥረቶች እንደሚደረጉ አመልክቷል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዲሬክተር እና የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ባለፈው እሑድ በሰጡት መግለጫ፣ በእንቅስቃሴው እየተሳተፉ ያሉ ኹሉ፣ ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
በአፍሪካ ሁለተኛ የሕዝብ ብዛት ባላት ኢትዮጵያ፣ እንደ ዐዲስ አለመረጋጋት የተቀሰቀሰው፣ በአጎራባቹ ትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት የተካሔደው አስከፊ ጦርነት ካበቃ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ነው። በዚኽ ጦርነት፣ የዐማራ ተዋጊዎችም ተሳትፈው ነበር።
ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር፣ የፌዴራል መንግሥት፣ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የክልል ልዩ ኀይሎችን ወደ ጸጥታ ተቋማት መልሶ ማደራጀት እንደጀመረ ማስታወቁን ተከትሎ፣ ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን፣ የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል። ውሳኔው፣ “ክልላችንን ያዳክማል፤” የሚሉ የዐማራ ብሔርተኞችን ተቃውሞ ያሥነሳ ሲኾን፣ የውጭ መንግሥታትም ለዜጎቻቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።
በሌላ በኩል፣ በዐማራ ክልል የበርካታ ከተሞች ነዋሪዎች፣ የፋኖ ታጣቂዎች ከፌደራል መንግሥቱ ኀይሎች ጋራ ግልጽ ግጭት ውስጥ መግባቱን፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል። ተስፋሁን የተባለ አንድ የባሕር ዳር ነዋሪ፣ እስከ ሰኞ እኩለ ለሊት ድረስ፣ “በአየር ማረፊያው መንገዶች ዙሪያ፣ የማያቋርጥ የተኩስ ድምፅ መስማቱን” ለዜና ተቋሙ ገልጿል፡፡ “ዛሬ ጠዋት፣ ልደታ 14 አካባቢ፣ የተኩስ ድምፅ ነበር፤” ሲል፣ በአየር መንገዱ አቅራቢያ በሚገኝ ሰፈር፣ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተስፋሁን አመልክቷል።
በቤት ውስጥ መቆየት በራሱ አስፈሪ ነው፤ ምክንያቱም የከባድ መሣሪያ ድምፆቹ በራሳቸው በጣም አሠቃቂ ናቸው፤... ይህ አስከፊ ኹኔታ እንዴት እንደሚያበቃ አላውቅም፤”
ስማቸው የተባለ በጎንደር ከተማ የሚኖር አሽከርካሪ በበኩሉ፣ “ሰዎች በየቤታቸው ውስጥ ናቸው። ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ የለም፤” ብሏል፡፡ “ነገሮች በጣም መጥፎ ኹኔታ ላይ ናቸው። ከተኩስ ልውውጥ በተጨማሪ ከባድ መሣሪያዎችም ከተማ ውስጥ አሉ፤” በማለትም ኹኔታውን አስረድቷል።
ስማቸው አክሎም፣ “በቤት ውስጥ መቆየት በራሱ አስፈሪ ነው፤ ምክንያቱም የከባድ መሣሪያ ድምፆቹ በራሳቸው በጣም አሠቃቂ ናቸው፤... ይህ አስከፊ ኹኔታ እንዴት እንደሚያበቃ አላውቅም፤” በማለት ስጋቱን ገልጿል።
በአንጻሩ፣ በ12ኛው እና በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተገነቡት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) የተመዘገቡት ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ የሚታወቀው የላሊበላ ከተማ፣ የተረጋጋ እንደኾነ፣ አንድ ሌላ ነዋሪ ገልጿል። “እዚኽም እዚያም የተኩስ ድምፅ እንሰማለን፤” ያለው ነዋሪው፣ ኹኔታው፣ ትላንት ጠዋት እንደነበረው አለመቆየቱን አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት፣ የፋኖ ተዋጊዎች፣ የላሊበላ ከተማንና የሽምሽሃ አየር ማረፊያን ተቆጣጥረው የነበረ ሲኾን፣ በሳምንቱ መጨረሻ ባለሥልጣናት፣ በክልሉ ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር፣ ተጠያቂ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አስታውቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ፣ በክልሉ የተከሠተው ግጭት፣ የሰብአዊ ረድኤት እንቅስቃሴዎችን አስቸጋሪ አድርጓቸዋል፤ ብሏል። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትም፣ ግጭቱ እንዳሳሰበው የገለጸ ሲኾን፣ አውስትራሊያ፣ ብሪታኒያ እና ስፔይን፥ ዜጎቻቸው ወደ ዐማራ ክልል እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ በማውጣት አሳስበዋል።
መድረክ / ፎረም