በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዐማራ ክልል ከተሞች የተኩስ ድምፅ መሰማቱ ቀጥሏል


ፎቶ ፋይል፦ ባሕር ዳር ከተማ
ፎቶ ፋይል፦ ባሕር ዳር ከተማ

· አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ከቁጥጥሩ ውጪ እንደኾኑ መንግሥት አስታወቀ

በዐማራ ክልል የጎንደር፣ ላሊበላ፣ ደብረ ብርሃንና ዋናዋ መዲና ባሕር ዳር ከተሞች፣ ዛሬ ሰኞም፣ የተኩስ ድምፅ እየሰሙ እንደኾነ፣ ነዋሪዎች አሶሽየትድ ፕሬስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

“የደብረ ብርሃን ከተማ የጦር አውድማ ኾናለች፡፡ በየደቂቃው የተኩስ ልውውጥ አለ፤” ሲሉ፣ አንድ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማው ባለሥልጣን ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል፡፡

የፋኖ ታጣቂዎች፣ ዋና ዋና የቱሪስት ከተሞች የኾኑትን ጎንደርንና ላሊበላን እንደተቆጣጠሩ፣ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ዛሬ ሰኞ ማለዳ፣ በላሊበላ ከተማ ዳርቻ፣ በአየር ማረፊያው አቅጣጫ የተኩስ ድምፅ እንደነበር የከተማዪቱ ነዋሪ ተናግሯል።

የፌዴራል ኃይሎች በፋኖ ታጣቂዎች የተያዙ ከተሞችንና ተቋማትን መልሰው ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት፣ ከጎንደር በስተሰሜን አቅጣጫ ከፍተኛ ውጊያ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“ተኩስ ይሰማናል፤ ጢስም ይታየናል፤” ሲል፣ አንድ የጎንደር ነዋሪ ተናግሯል። በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር የዋሉ የሥፍራው ባለሥልጣናትም፣ በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው እንደሚገኙ፣ ነዋሪው ጨምሮ ገልጿል።

በባሕር ዳር ሰማይ ላይ፣ የወታደራዊ አውሮፕላኖች ድምፅ እንደሚሰማ፣ እንዲሁም የከተማው የውኃ አገልግሎት እንደተቋረጠ፣ አንድ ነዋሪ ተናግሯል። ሌላው ነዋሪም፣ ታንኮች ወደ ከተማው እየገቡ እንደኾነ ተናግሯል። “የነገሮች መበላሸት ተባብሶ ቀጥሏል። ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ድምፅ ይሰማል፤” ሲል ተናግሯል።

“መደበኛ ያልኾኑ የዐማራ ኀይሎች ከተሞችን ተቆጣጥረዋል፤ እስረኞችን ለቀዋል፤ የመንግሥት ተቋማትንም ተቆጣጥረዋል፤” ሲሉ፣ በአስቸኳይ ዐዋጁ አፈጻጸም ላይ፣ ትላንት እሑድ ምሽት፣ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዲሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።

“ኀይሎቹ የክልሉን መንግሥት ካፈረሱ በኋላ፣ ወደ ፌዴራሉ መንግሥት የመምጣት ፍላጎት አላቸው፤” ሲሉ ከሠዋል አቶ ተመስገን ጥሩነህ።

የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል ኀይሎችን ከአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ጋራ ለማዋሐድ ዕቅድ ማውጣቱን ተከትሎ፣ በዐማራ ክልል ውጥረት እና ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል። ከዚኽ በኋላ መንግሥት፣ ባለፈው እሑድ፣ በክልሉ እስከ ስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚኾን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አውጥቷል። በዐማራ ክልል ያሉ ነዋሪዎች እና የክልሉ ኃይሎች፣ “የፌዴራሉ መንግሥት ክልሉን ለማዳከም እያሰበ ነው፤” በሚል ይከሣሉ። መንግሥት በበኩሉ፣ “በክልሉ በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ኀይሎች፣ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ስጋት ናቸው፤” ይላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ባለፈው ዐርብ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ በስልክ መነጋገራቸውን አስታወቀው፣ እየተበላሸ የመጣው የጸጥታ ኹኔታ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ፣ በዐማራ ክልል ያለው ግጭት፣ የሰብአዊ ሥራውን እያወከ ነው፤ ብሏል። ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንዲኖርና የጤና ተቋማት እንዲጠበቁ፣ የድርጅቱ ዲሬክተር ጄኔራል ዶር. ቴድሮስ አድኀኖም ጥሪ አቅርበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG