በርዳታ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ እህል “ተሰርቋል” በሚል፣ ከአራት ወራት በፊት፣ በኢትዮጵያ፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የሚሰጠውን የምግብ ርዳታ ያቋረጠው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ቀስ በቀስ ርዳታውን ዳግም ማሰራጨት እንደጀመረ ታውቋል።
በአንዳንድ ቦታዎች፣ በአነስተኛ መጠን ርዳታ በማከፋፈል ላይ እንደኾነ የገለጸው ፕሮግራሙ፣ በማሠራጨቱ ሒደት ውስጥ፣ መንግሥት፣ አሁንም ሚና እንዳለው አስታውቋል።
ርዳታው መቋረጡ፣ “ኢሞራላዊ ውሳኔ ነው፤” ሲሉ፣ የነቀፉ ሌሎች የሰብአዊ ርዳታ ድርጅቶች እና የጤና ሠራተኞች፣ በማቋረጥ ውሳኔው ምክንያት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረኀብ ሞተዋል፤ ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በበኩሉ፣ በአካባቢ ባለሥልጣናት ቁጥጥር ሥር የነበረውን የርዳታ እደላ አስመልክቶ፣ ከመንግሥት ጋራ እየተደራደረ በመኾኑ፣ የምግብ ርዳታ የማቋረጡ ውሳኔ አሁንም በተግባር ላይ እንዳለ አስታውቋል።
የምግብ ርዳታ መቋረጡ፣ 20 ሚሊዮን የሚኾኑ ወይም ከአጠቃላይ ሕዝቡ አንድ ስድስተኛውን ሕዝብ፣ እንዲሁም 800 ሺሕ ስደተኞችን ችግር ላይ ጥሏል፤ ተብሏል።
ከአሶሺዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ለቀረበለት ጥያቄ፣ የጽሑፍ መልስ የሰጠው፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መቶ ሺሕ ለሚኾኑና በሰሜን ትግራይ አራት አውራጃዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች፣ ካለፈው የፈረንጆች ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ፣ ስንዴ ማሰራጨት መጀመሩን አስታውቋል። “የምግብ ርዳታውን ለማድረስ፣ የተሻለ ቁጥጥር ያለበትን አሠራር” በመሞከር ላይ እንደሚገኝ ፕሮግራሙ አስታውቋል።
ዐዲሱ አሠራር፡- ተጠቃሚዎችን በዲጂታል መመዝገብ፣ የምግብ ጆንያ ላይ ምልክት ማድረግ፣ ግብረ መልስ የሚቀበልበት የስልክ መሥመር መዘርጋት፣ እንዲሁም ለአጋር ድርጅቶች ሥልጠና መስጠትን እንደሚጨምር፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል። ዐዲሱን ዐሠራር፣ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም ተግባራዊ ለማድረግ ተስፋ እንዳለው ያመለከተው ፕሮግራሙ፣ ይህም፣ “ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች ብቻ ለማድረስ ያስችላል፤” ሲል እምነቱን ገልጿል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ለርዳታ የገባ እህል መሰረቁን አረጋግጫለኹ፤ ማለቱን ተከትሎ፣ ባለፈው ወርኀ መጋቢት፣ ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን ርዳታ አቋርጦ ነበር። በአንዲት የትግራይ ከተማ ብቻ፣ 134ሺሕ ሰዎችን፣ ለአንድ ወር መመገብ የሚችል ምግብ ተሰርቆ ለገበያ መቅረቡን ፕሮግራሙ ገልጿል። እህሉ፥ አሜሪካዊ መለዮ ካለበት መሸከፊያው ጭምር ለገበያ ቀርቦ ነበር፤ ብሏል ፕሮግራሙ። ባለፈው ሰኔ ደግሞ፣ አሜሪካ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የምግብ ርዳታ ሥርጭቱን፣ በመላ ኢትዮጵያ እንዲቋረጥ መወሰናቸው ይታወሳል።
መድረክ / ፎረም