በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአማራ ክልል “የዘፈቀደ ግድያ እንዲቆምና ፈጻሚዎቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ” አምነስቲ ጠየቀ


በአማራ ክልል “የዘፈቀደ ግድያ እንዲቆምና ፈጻሚዎቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ” አምነስቲ ጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:22 0:00

በአማራ ክልል “የዘፈቀደ ግድያ እንዲቆምና ፈጻሚዎቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ” አምነስቲ ጠየቀ

የኢትዮጵያ የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ እና መስከረም ወራት፣ በባሕር ዳር ከተማ 12 የሚደርሱ ሲቪሎችን ከሕግ ውጭ ገድለዋል፤ ሲል፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ዛሬ ሰኞ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ ይፈጸማል ያለውን ግድያ እንዲያስቆምና ግድያ የፈጸሙትንም ለሕግ እንዲያቀርብ ድርጅቱ ጥሪ አድርጓል።

የአምነስቲን ሪፖርት አስመልክቶ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስተያየት እንዲሰጡ ሞክረን ለማግኘት አልቻልንም።

የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ዛሬ ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርቱ እንዳስታወቀው፣ የፌዴራል የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲሁም መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአማራ ክልል መዲና በባሕር ዳር ከተማ፣ በድምሩ 12 ሲቪሎችን ከሕገ ውጪ ገድለዋል፤ በአንዳንዶቹም ግድያዎች ወቅት የቤተሰብ አባላት አስከሬኖችን አንሥተው እንዳይቀብሩ መከልከላቸውን ገልጿል።

የዛሬው የአምነስቲ ኢንተርናሽል ሪፖርት፤ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት አስመልክቶ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት የወጣ የመጀመሪያው ሪፖርት እንደሆነ ተመልክቷል።

“ሊዋጓቸው ከመጡት ወገኖች ጋራ የሚዋጉ እንጂ፣ እኛን ሊወጉን የመጡ አልመሰለንም ነበር” የሚለውንና በሕይወት ከተረፉት ሰዎች እማኝነት የተቀነጨበውን የምስክርነት ቃል፣ የሪፖርቱ ርእስ ያደረገው የመብቶች ድርጅቱ፤ “ኢትዮጵያ ፣ በአማራ ክልል ያለውን ከሕግ ውጪ የሚፈጸም ግድያ አቁሚ፣ ግድያ የፈፀሙትንም ለሕግ አቅርቢ” ሲል ጥሪ አድርጓል።

ሪፖርቱ፤ ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በባሕር ዳር ቀበሌ 14 በአቡነ ሐራ እና ልደታ መንደሮች ስድስት ሲቪሎች፤ እንዲሁም ከሁለት ወራት በኋላ፣ በመስከረም 29 እና 30 ቀናት 2016 ዓ.ም. በከተማዋ ሰባ ታሚት መንደር ስድስት ሌሎች ሲቪሎች፣ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ከሕግ ውጪ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ሰንዷል።

የመብቶች ድርጅቱ የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዲሬክተር ቲጌሬ ቻጉታ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በባሕር ዳር ከተማ እና በአጠቃላይ በአማራ ክልል እየተካሔደ ካለው ግጭት ጋራ በተያያዘ በሚታየው “የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” ጉዳይ፣ በአስቸኳይ ውጤታማ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሒድ ጠይቀዋል፡፡ “ሁከቱን በመፈጸም በተጠረጠሩት ሰዎች ላይ በቂ ማስረጃ” መኖሩን የጠቀሱት ዲሬክተሩ፣ “ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፤” ብለዋል። ክሱ እና የፍርድ ሒደቱም፣ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የፍርድ ሒደትን በተከተለና የሞት ቅጣት ውሳኔን መስጠት ሳያስፈልግ እንዲካሔድ ጥሪ ማድረጋችውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸውና በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ዘመቻ አስተባባሪ የሆኑት ሱዐድ ኑር ባስተላለፉት ጥሪም፣ የኢትዮጵያ የፌዴራሉ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሲቪሎችን ዒላማ ማድረግ እንዲያቆሙና ባለሥልጣናትም ስለተፈጸመው ግድያ ምርመራ እንዲያደርጉና ተጠያቂዎችን ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

አክለውም “በኢትዮጵያ በሕግ ያለመጠየቅ አካሔድ መቀጠሉን ያመለከተው የአምነስቲ ሪፖርት፣ በዓለም አቀፍ ሕግ በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊትን ጭምር የሚፈጽሙ ሰዎችን እያበረታታ ነው። ተኣማኒነት ያለው ፍትሕ የማይኖር ከሆነ ማኅበረሰቡ አደጋ ላይ ይወድቃል። ወንጀልን መቀነስም አይቻልም” ሲሉ አሳስበዋል።

ሱዐድ አያይዘውም ፣ “በትግራይ ያልታጠቁ ነዋሪዎች እንደተገደሉ ያመለከተውንና ከዚህ ቀደም ያወጣነውን ሪፖርት ጨምሮ ሌሎችም ሪፖርቶች የሚያመለክቱት፣ ሲቪሎች ዒላማ መሆናችው እንደቀጠለና መብታቸው በመጣስ ላይ መሆኑን ነው። የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎችም መብቶቻቸው በግጭት ምክንያት ይገደባሉ። በመሆኑም፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ አካላት፣ በተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ ያቀረበውን የምርመራ ውጤት በአፋጣኝ እንዲጤኑና ከምርመራው ውጤት ጋራ የሚጣጣም ሒደት እንዲጀምሩ እንጠይቃለን” ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ከዐይን እማኞች እና ከሰለባዎቹ ቤተሰቦች አገኘሁት ባለው መረጃ፣ ግለሰቦቹ የተገደሉት በቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት ተመተው መሆኑን በሪፖርቱ አስፍሯል።

ልደታ በተባለው አካባቢ አቅራቢያ፣ ይታጠቁ አያሌው የተባለች ግለሰብ፣ በአንድ የፌዴራሉ መከላከያ ሠራዊት አባል በቤቷ ሳለች መገደሏን፣ አንድ የ17 ዓመት ዘመዷን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የዐይን ምስክሮች መናገራቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ለደኅንነቱ ሲባል ማንነቱ እንዳይታወቅ ‘ቢኒያም’ በሚል ተለዋጭ ስም በሪፖርቱ የተጠቀሰው የ17 ዓመቱ የሟች ዘመድ፤ ይታጠቁ አያሌው፥ ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በመኖሪያ ግቢ ውስጥ እንጀራ በመጋገር ላይ ሳለች፣ ወታደሮቹ በግቢው አጥር ክፍተት በኩል አሾልከው ወደ ግቢው ሲተኩሱ እንደተገደለች ምስክርነቱን ሰጥቷል። በዙሪያው የሚካሔደውን ተኩስ እንደሰሙ ይታጠቁ መጋገሯን አቋርጣ ወደ ቤት እንድትገባ በግቢው ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢነግሯትም፣ “ልጄ የሚበላው ቁርስ የለም፤ ትንሽ ነው የቀረኝና ጋግሬ መጨረስ አለብኝ፤” ብላ መጋገሯን ቀጠለች፤ በኋላም ምናልባትም በአካባቢው አንድን ግለሰብ በማሳደድ ላይ የነበሩ ወታደሮች ወደ ግቢው መተኩሳቸውን፣ ‘ቢኒያም’ በሚል የተጠቀሰው የሟች ዘመድ አስረድቷል።

አየነው ደፍረሽ የተባለ የ55 ዓመት ግለሰብ እና ካሳሁን እና አብርሃም በሚል የሚጠሩ ልጆቹ፣ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤት በሚመለሱበት ወቅት በጥይት ተመተው እንደተገደሉ፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አስታውቋል። የሟቾች ቤተሰብ አባል በሰጠው ምስክርነት፣ ወደ አየነው ስልክ ላይ ሲደውሉ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባል እንደሆነ የሚያምኑት ሰው ስልኩን አንሥቶ፣ “አነስ ያለ አደጋ ተከሥቷል፤” ብሎ እንደመለሰላቸው መናገሩን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ሰባ ታሚት በተባለው ስፍራ እንደተካሔደ በተገለጸው ውጊያ ወቅት ደግሞ፣ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ስድስት ሰዎች ከሕግ ውጪ ተረሽነው መገደላቸውን አምነስቲ እንዳረጋገጠ በሪፖርቱ ተመልክቷል። ከተገደሉት አንዱም በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ ጤና ጣቢያ የነበረ ታካሚ መሆኑን፣ በዚሁ ጤና ጣቢያ የሚገኙ ሠራተኞችንም የሠራዊቱ አባላት እንደደበደቧቸውና መሣሪያ ደቅነው እንዳስፈራሯቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።

አሁንም በዚያው በሳባ ታሚት አካባቢ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ማለዳ፣ ታደሰ መኰንን ወደተባሉ የ69 ዓመት ነዋሪ ቤት በመግባት ሦስት ልጆቻቸውንና የቤታቸውን አንድ ክፍል ተከራይቶ ይኖር የነበረን ሌላ ግለሰብ እንደረሸኑ፣ አምነስቲ ከሦስት ግለሰቦች ጋራ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ጠቅሶ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

ወታደሮቹ ሦስቱን ወንድማማቾች እና በቤታቸው የሚኖርን አንድ ግለሰብ ከመግደላቸው በፊት በዱላ እንደደበደቧቸው፣ በኋላም አንደኛው ወታደር “ማንንም ሳታስቀሩ ሁሉም ላይ ተኩሱ” ማለቱን፣ ለደኅንነታቸው ሲሉ እውነተኛ ስማቸውን በመደበቅ ‘ካሳ’ በሚል አምነስቲ በሪፖርቱ የጠቀሳቸው አንድ የአቶ ታደሰ መኰንን ዘመድ መስክረዋል።

ቀሪ የቤተሰቡ አባላት አስከሬኖቹን እንዳያነሡ ወታደሮቹ መከልከላቸውን፣ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ ቀኑ ዐሥር ሰዓት ድረስ፣ አስከሬኖቹ መንገድ ላይ ውለው ወታደሮቹ ከስፍራው ሲሔዱ እንደተነሡ፣ ‘ካሳ’ በሚል የተጠሩት ግለሰብ እና ሌሎች ሦስት ምስክሮች መናገራቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ገዳዮቹ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሆናቸውን እንዴት እንዳወቁ አምነስቲ ያነጋገራቸውን ምስክሮች መጠየቁንና በምላሹም፣ በአማራ ክልል ግጭቱ ከመጀመሩ ሦስት ወራት ቀደም ብሎም የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ በክልሉ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር፣ የለበሱትንም ወታደራዊ ዩኒፎርም ለይተው እንደሚያውቁ መናገራቸውን በሪፖርቱ አስፍሯል።

አንዳንዶቹ ወታደሮችም፣ “መሣሪያችሁን አምጡ፤ ፋኖን ትደግፋላችሁ?” ሲሉ የሰለባዎቹን ቤተሰቦች ይጠይቁ እንደነበር በሪፖርቱ አመልክቷል።

በአማራ ክልል ያለው የትጥቅ ግጭት በሰብአዊ መብቶች ላይ ያስከተለው ጫና ይፋ ለመሆን ጊዜ መውሰዱን ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ ምክንያቶቹ ደግሞ፡- የኢንተርኔት መዘጋት እና ሌሎች የግንኙነት መንገዶች መቋረጥ፣ አሁንም ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የሰዎችን የመናገር ነጻነትንም ሆነ የብዙኀን መገናኛን ሥራ በመገደቡና ሰዎችም በቀልን በመፍራት ስለማይናገሩ እንደሆነ፣ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ በሪፖርቱ አብራርቷል።

በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ፣ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት የወጣ የመጀመሪያ ሪፖርት መሆኑን የጠቆሙት፣ በአምነስቲ የአፍሪካ ቀንድ ዘመቻ አስተባባሪው ሰዑድ ኑርም፣ መረጃውን በመሰብሰብ ረገድ ስለነበረው ተግዳሮት እና ወደፊትም መሥራት ስላቀዱት ያወሳሉ።

“ምርመራችን የተመለከተው በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ የተፈጸሙትንና የተወሰኑ ግድያዎችን እንጂ፣ የክልሉን አጠቃላይ ችግር አያመለክትም። በምርመራችን የተጠቀምነው ዘዴ ለእያንዳንዱ ግድያ ‘ከፍተኛ ማስረጃን’ የሚጠይቀውን ዘዴ ነው። በአጠቃላይ መረጃዎቹን ለማጠናቀር ውስብስብና አዳጋች ነበር። ይህ ሪፖርት በክልሉ ያለውን የመብቶች ጥሰት አስመልክቶ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት የወጣ የመጀመሪያ ሪፖርት ነው። በክልሉም ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በሚታዩት የመብቶች ጥሰቶች ጉዳይ መሥራታችንንና ማጋለጣችንን እንቀጥላለን። ኢንተርኔት በሌለበትና ከአደጋው የተረፉትም ሆነ የዓይን ምስክሮች በቀልን በመፍራት ምስክርነታቸውን መስጠት በሚፈሩበት ሁኔታ የተዘጋጀ ነው። በክልሉም ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በሚታየው የትጥቅ ግጭት ጋራ በተያያዘ መሥራታችንን እንቀጥላለን።”

በጉዳዩ ላይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማናገርና አስተያየቱን ለማካተት መሞከራቸውን ነገር ግን ምላሽ እንዳላገኙ ሱዐድ ኑር ጨምረው ገልጸዋል።

በኛም በኩል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉንና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩምን ለማግኘት በስልክ እና በጽሑፍ ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG