በዐማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ከታወጀ ወዲህ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደው፤ የክልሉ ምክር ቤት አቶ አረጋ ከበደን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል።
ክልሉን ለሁለት ዓመታት ያህል የመሩት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ሥራቸውን “በማኅበራዊ ቤተሰባዊና ጤና ምክንያቶች በፍቃዳቸው” መልቀቃቸው ተገልጿል።
አዲሱ የክልሉ ፕሬዚዳንት፣ አቶ ከበደ፣ የክልሉ የሥራና ሥልጠና ቢሮ ኃላፊ ነበሩ። ዶ/ር ከፋለን የጠቀሰው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘገባ “ሕዝብና መንግሥት የጣሉባቸውን ኃላፊነት በገባቸውና በቻሉት ልክ ተወጥቻለሁ ብለው እንደሚያምኑ” አመልክቷል።
ክልሉ የገባበትን የፀጥታ ችግር በተመለከተም “ከግጭት በፊት ክልሉ ያሉበትን ጉዳዮች ማጤን ይገባ ነበር” ያሉት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር “ኃይል አማራጭ ሊሆን እንደማገባው”ም መክረዋል።
ከመንግሥት ውጭ የታጠቀ ኃይል መኖር እንደሌለበት እንደሚያምኑ የተናገሩት ተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር የዚህ ዓይነቱ አካሄድ መጨረሻው "እንደ የመንና እንደ ሶማሊያ ወደመሆን እንደሚወስድ” አሳስበዋል።
በ2010 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ጊዜ አንስቶ የአማራ ክልል አዲስ ርዕሰ መስተዳድር ሲሾም የአሁኑ ስድስተኛ ጊዜ መሆኑን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና የዓለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ያያው ገነት ቸኮል አስታውሰዋል። ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም