በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን እንዳይውል አምነስቲ ጠየቀ


ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ካርታ
ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ካርታ

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን እንዲሁም መንግሥትን የሚነቅፉ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎችን እና ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ ለማሰር፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን እንደ ምክንያት በመጠቀም ላይ ናቸው ሲል የሰብአዊ መብት ቡድኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ አስታውቋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በክልሉ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ባለፈው ነሐሴ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ “ለባለሥልጣናት ያልተገደበ ሥልጣን በመስጠቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በመላ አገሪቱ ሰዎች ካለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ታስረዋል፣ ሰዓት እላፊ ተጥሎ የሰዎች የመንቀሳቀስ እንዲሆም የመሰብሰብ መብት ተገፏል” ሲል የሰብዓዊ መብት ቡድኑ ገልጿል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከሁለት ሳምንታት በፊት መራዘሙ ይታወሳል።

“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ መሠረታዊ መብትን ለማገድ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅን ሰበብ የማድረግ የተለመደ ዘዴ መጠቀምን ሊያቆሙ ይገባል” ያሉት የአምነስቲ ኢንተርናሽንል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዲሬክተር ታይገሪ ቻጉታ፣ “ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ሌላ ግጭት፣ በትግራይ የሰብዓዊ ቀውስ፣ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር በኦሮሚያ፣ በመላ አገሪቱ ደግሞ በሕግ ያለመጠየቅ እና ያለመከሰስ ሁኔታ የሚታይባት አገር ሆናለች” ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃንና ሃሳብን የመግለጽ መብት አሁንም አስፈላጊ እንደሆኑ ያስታወሱት ኃላፊው፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መራዘም እስከ አሁን በነጋሪት ጋዜጣ አለመታተሙን፣ ግልጸኝነት ያለመኖር መረጃ የማግኘትን መብት እንደሚጥስ፣ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውን ምን ሲፈጽሙ እንደ ወንጀል እንደሚቆጠርባቸው እንደማያውቁ፤ በተጨማሪም አዋጁ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ መሆኑን በግልጽ እንደማያውቁ ቻጉታ የመብት ድርጅቱ በወጣው መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

ፖለቲከኞች እና ሦስት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ ዋጁ ተይዘው እንደሚገኙ ከቤተሰባቸው ማረጋገጡን የጠቀሰው አምነስቲ፣ ከነዚህም ውስጥ የፓርላማ አባሉ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ም/ቤት አባሉ ካሳ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ም/ቤት አባሉ ዮሐነስ ቧያለው፣ የሰላም ሚኒስትሩ ታዬ ደንዳአ እንደሚገኙበት ዘርዝሯል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከተራዘመ ወዲህ ደግሞ የፓርላማ አባሉ ደሳለኝ ጫኔ መያዛቸውን ጨምሮ አስታውሷል።

በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መሠረት በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ተይዘው፣ በርካቶቹ ትምሕርት ተሰጥቷቸው እንደተለቀቁ እንዲሁም በመቶ የሚቆጠሩ አሁንም በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ለፓርላማ ማረጋገጣቸውን አምነስቲ ጨምሮ አስታውሷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG