በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአማራ ክልል “የዘፈቀደ ግድያ እንዲቆምና ፈጻሚዎቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ” አምነስቲ ጠየቀ


በአማራ ክልል “የዘፈቀደ ግድያ እንዲቆምና ፈጻሚዎቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ” አምነስቲ ጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:22 0:00

የኢትዮጵያ የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ እና መስከረም ወራት፣ በባሕር ዳር ከተማ 12 የሚደርሱ ሲቪሎችን ከሕግ ውጭ ገድለዋል፤ ሲል፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ዛሬ ሰኞ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ ይፈጸማል ያለውን ግድያ እንዲያስቆምና ግድያ የፈጸሙትንም ለሕግ እንዲያቀርብ ድርጅቱ ጥሪ አድርጓል።

የአምነስቲን ሪፖርት አስመልክቶ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስተያየት እንዲሰጡ ሞክረን ለማግኘት አልቻልንም።

የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ዛሬ ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርቱ እንዳስታወቀው፣ የፌዴራል የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲሁም መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአማራ ክልል መዲና በባሕር ዳር ከተማ፣ በድምሩ 12 ሲቪሎችን ከሕገ ውጪ ገድለዋል፤ በአንዳንዶቹም ግድያዎች ወቅት የቤተሰብ አባላት አስከሬኖችን አንሥተው እንዳይቀብሩ መከልከላቸውን ገልጿል።

የዛሬው የአምነስቲ ኢንተርናሽል ሪፖርት፤ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት አስመልክቶ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት የወጣ የመጀመሪያው ሪፖርት እንደሆነ ተመልክቷል።

“ሊዋጓቸው ከመጡት ወገኖች ጋራ የሚዋጉ እንጂ፣ እኛን ሊወጉን የመጡ አልመሰለንም ነበር” የሚለውንና በሕይወት ከተረፉት ሰዎች እማኝነት የተቀነጨበውን የምስክርነት ቃል፣ የሪፖርቱ ርእስ ያደረገው የመብቶች ድርጅቱ፤ “ኢትዮጵያ ፣ በአማራ ክልል ያለውን ከሕግ ውጪ የሚፈጸም ግድያ አቁሚ፣ ግድያ የፈፀሙትንም ለሕግ አቅርቢ” ሲል ጥሪ አድርጓል።

ሪፖርቱ፤ ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በባሕር ዳር ቀበሌ 14 በአቡነ ሐራ እና ልደታ መንደሮች ስድስት ሲቪሎች፤ እንዲሁም ከሁለት ወራት በኋላ፣ በመስከረም 29 እና 30 ቀናት 2016 ዓ.ም. በከተማዋ ሰባ ታሚት መንደር ስድስት ሌሎች ሲቪሎች፣ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ከሕግ ውጪ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ሰንዷል።

የመብቶች ድርጅቱ የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዲሬክተር ቲጌሬ ቻጉታ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በባሕር ዳር ከተማ እና በአጠቃላይ በአማራ ክልል እየተካሔደ ካለው ግጭት ጋራ በተያያዘ በሚታየው “የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” ጉዳይ፣ በአስቸኳይ ውጤታማ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሒድ ጠይቀዋል፡፡ “ሁከቱን በመፈጸም በተጠረጠሩት ሰዎች ላይ በቂ ማስረጃ” መኖሩን የጠቀሱት ዲሬክተሩ፣ “ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፤” ብለዋል። ክሱ እና የፍርድ ሒደቱም፣ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የፍርድ ሒደትን በተከተለና የሞት ቅጣት ውሳኔን መስጠት ሳያስፈልግ እንዲካሔድ ጥሪ ማድረጋችውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸውና በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ዘመቻ አስተባባሪ የሆኑት ሱዐድ ኑር ባስተላለፉት ጥሪም፣ የኢትዮጵያ የፌዴራሉ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሲቪሎችን ዒላማ ማድረግ እንዲያቆሙና ባለሥልጣናትም ስለተፈጸመው ግድያ ምርመራ እንዲያደርጉና ተጠያቂዎችን ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

አክለውም “በኢትዮጵያ በሕግ ያለመጠየቅ አካሔድ መቀጠሉን ያመለከተው የአምነስቲ ሪፖርት፣ በዓለም አቀፍ ሕግ በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊትን ጭምር የሚፈጽሙ ሰዎችን እያበረታታ ነው። ተኣማኒነት ያለው ፍትሕ የማይኖር ከሆነ ማኅበረሰቡ አደጋ ላይ ይወድቃል። ወንጀልን መቀነስም አይቻልም” ሲሉ አሳስበዋል።

XS
SM
MD
LG