በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን በታጣቂ ኃይሎች መካከል ግጭቱ ተባብሶ ቀጥሏል


ሱዳን ሚያዚያ/2015
ሱዳን ሚያዚያ/2015

ትላንት ቅዳሜ ጠዋት ሚያዚያ 07/2015 ሳፍ በሚል ምህጻረ ቃል በሚታወቁት በሱዳን ታጣቂ ሃይሎች እና በአጣዳፊ የድጋፍ ሃይሎች አር.ኤስ.ኤፍ ሚሊሺያዎች መካከል የተጀመረው ግጭት በካርቱም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። ግጭቱ እንደ ዳርፉር ወዳሉ ከተሞችም እየተስፋፋ መሄዱ ተነግሯል።

በሱዳን መዲና በካርቱም ከባድ የሆኑ ታንኮች፣ መድፎች፣ እና የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውም ተዘግቧል። ግጭቱ የሽግግር መንግስት ምስረታን በተመለከተ ውጥረት የተሞላበት ለሳምንታት የዘለቀ ውይይትን ተከትሎ የተከሰተ ነው።

የአለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ግጭቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪሎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚደረግ በመሆኑ የግጭቱ ተሳታፊዎች በሙሉ ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብሩ ጥሪ አድርጓል። በሌላ የተያያዘ ዜና በግጭቱ ሶስት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሰራተኞች በሰሜናዊ ዳርፉር አካባቢ በስራ ላይ ሳሉ ህይወታቸው አልፏል።

በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቀናጀ የሽግግር እርዳታ ልዑክ ዩኒታምስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቮልከር ፐርቴስ ሰብዓዊ ድጋፍ ሲሰጡ በነበሩት የመንግስታቱ ድርጅት ሰራተኞች ላይ የደረሰውን ጉዳት አውግዘዋል።

ዋና ሃላፊው ባወጡት መግለጫም “የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን የማጥቃት አዝማሚያ መኖሩ በጣም አስደንግጦኛል።” ያሉ ሲሆን አያይዘውም “ሲቪሎች እና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጡ የእርዳታ ተቋማት ሰራተኞች ዒላማ አይደሉም” ሲሉ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ በሱዳን ሃይሎች መካከል እየተባባሰ የመጣው ግጭት እንዳሳሰባቸው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ አስታውቀዋል። ዋና ጸሃፊው በእርዳታ ሰራተኞቹ ላይ የደረሰውን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉ በአስቸኳይ ግጭቱን አቁመው ወደ ውይይት እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል፤ ሲሉ የዋና ጸሃፊው ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG