በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደራዳሪነት በየመን ተፋላሚ ወገኖች መካከል ለሰኞ ተይዞ የነበረው የሰላም ድርድር ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ተዘገበ።
በኩዌት በዛሬው እለት ሊጀመር ታቅዶ የነበረው የመናዊ-ከየመናዊ የተባለው የሰላም ድርድር በየመን የመንግሥታቱ ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ኢስማኢል ኦላድ ቼክ አህመድ(Ismail Ould Cheik Ahmed) ማብራሪያ፤ ባለፉት ጥቂት ሰዓታት በተከሰቱ ሁኔታዎች ሳቢያ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። የምክኒያቶቹን ተጨባጭ ምንነት ግን ልዩ መልዕክተኛው አልዘረዘሩም።
“የገጠሙትን ፈተናዎች ለማለፍ ጥረት በማድረግ ላይ ነን፤”ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት አደራዳሪ “ተደራዳሪዎች በሰላም ንግግሩ ለየመኑ ቀውስ አንዳች ሁነኛ እልባት ለማበጀት በሚያስችል በቅንነትና በትምምን ላይ የተመሠረተ ድርድር እንዲያካሂዱ ነው የምንጠይቀው፤” ብለዋል።
ኢስማኢል ኦላድ ቼክ አህመድ ቀጣዩ ጥቂት ሰዓታት ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተው። “ተደራዳሪ ወገኖች ያለባቸውን ኃላፊነት ከፍ አድርገው እንዲመለከቱና ሁሉን አቀፍ በሆኑ መፍትሄዎች ላይ እንዲስማሙ፤ ጥሪ እናደርጋለን፤” ሲሉ አክለዋል።
የየመን መንግስት ባለሥልጣናት፤ 18 ወራት ለዘለቀው፥ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች ለተገደሉበትና ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ላስከተለው ግጭት ማብቂያ ለማበጀት የታለመውን ድርድር ሂደት “ሆን ብሎ በማጓተት” ሁቲ አማጽያኑን ተጠያቂ አድርገዋል።
“ማንም የማያገል የፖለቲካ ሽግግር እውን ለማድረግ ተዘጋጅተናል። የሕስቡን ስቃይና ሰቆቃ ለመታደግም ያለንን ሁሉ ከመስጠት፤ የተቻለንን ሁሉ ከማድረግ አንቆጠብም።” ሲሉ የየመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አብደል ማሌክ ለመንግስታዊው የዜና ወኪል ሳባ ዛሬ ቀደም በሰጡት አስተያየት አመልክተዋል።
ለኪዌት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት፤ የዕርቅ መንፈስ ያንጸባረቁት የአማጺዊ ቡድን ቃል አቀባይ ሞሃመድ አብዱልሰላም በበኩላቸው፤ በሽግግሩ ወቅት በሚነሱ ማናቸውም የፖለቲካ ያለመግባባቶች ላይ ውሳኔ የሚሰጥ፤ “የሁሉንም ወገኖች ይሁንታ ያገኘ” ላሉት አካል ምሥረታ ጥሪ አድርገዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደራዳሪነት ባለፈው ዓመት ሁለት በየመን ተፋላሚ ወገኖች መካከል ለዛሬ ሰኞ ተይዞ የነበረው የሰላም ድርድር ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ተዘገበ።