የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፥ ናይጄሪያ ከቦኮ ሐራም (Boko Haram) ነውጠኞች ጋር በምታካሂደው ውጊያ የሚረዱ 24 ተቀባሪ ፈንጂዎችን የሚቋቋሙ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ሰጥቷል።
11 ሚሊዮን ዶላር የሚገመቱትን ተሽከርካሪዎች፥ በዛሬው እለት ሌጎስ የሚገኙት የናይጄሪያ ወታደራዊ ባለሥልጣናት መረከባቸውን በዚያ ከሚገኘው የአሜሪካ ቆንሲላ ጽሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ ያስረዳል።
ስጦታው ከቦኮ ሐራም(Boko Haram) ጋር የሚያካሂደውን ትርጉም የለሽ ሽብር እንዲከላከሉና ያካባቢውን ፀጥታ ጥበቃ እንዲያጠናክሩ፥ ዩናይትድ ስቴትስ ናይጄሪያና ጎረቤቶቿን ለመርዳት ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል ሲል ቆንሲላው ጨምሮ አስረድቷል።
ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ጥቅምት 300 ወታደሮችን ወደ ሰሜን ካሜሩን የላከች ሲሆን፥ ባለፈው ወር ደግሞ ተዋጊ ተሽከርካሪዎችን፥ ኅይል አመንጪ ጄኔሬተሮችንና ሌሎች በጦርነቱ የሚያግዙ መሣሪያዎችን ለግሳለች።
አንድ በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የሽብር ተግባር የሚከታተል ቡድን ባቀረበው ጥናት መሠረት፥ ቦኮ ሐራም(Boko Haram) በአውሮፓውያኑ ዓመት 2014 ብቻ 6,500 ሰዎችን በመግደል፥ በዓለም ግዙፉ አሸባሪ ቡድን ነው። ዝርዝሩን ለማዳመጥ ከዚህ በታች ያለውን የድምጽ ፋይል ይጫኑ።