የካሜሩን ወታደራዊ ሃይሎች 100 የቦኮ ሐራም አማጽያንን እንደገደሉና በጽንፈኛው ቡድን ተይዘው የነበሩ 900 ሰዎችን እንዳስለቀቁ ካሜሩን ገልጻለች።
ወታደሮቹ መሰረቱ ናይጀርያ የሆነውን ጽንፈኛ ቡድን አባላትን ገድለው ታጋቾቹን ያስለቀቁት ባለፈው ሳምንት በካሜሩንና በናይጀርያ ድንበር ላይ በተካሄደ እንቅስቃሴ እንደሆነ የካሜሩን የመከላከይ ሚኒስቴር ገልጿል። ይህ ዜና በነጻ ምንጭ አልተረጋገጠም።
በሌላ ዜና ደግሞ ትላንት ማታ በሰሜን ካሜሩን ቢያንስ የአራት ሰዎችን ህይወት ያጠፋ ጥንድ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት የፈጸመው ቦኮ ሐራም ነው የሚል ጥርጣሬ አላቸው የሀገሪቱ ባለስልጣኖች።
እስላማውያኑ አማጽያን ከሁለት አመታት በፊት ካሜሩን ላይ ድንበር ዘለል ጥቃት ማካሄድ ከጀምሩበት ጊዜ አንስቶ ሀገሪቱ ቦኮ ሐራምን ስትዋጋ ቆይታለች። ካሜሩን ጽንፈኛውን ቡድን ለመዋጋት ለተመሰረተ አምስት ሀገሮችን ላቀፈው ግብረ ሃይል ወታደሮች ካዋጡት ሃገሮች አንዷ ናት።
ቦኮ ሐራም በሰሜን ናይጀርያ ጥብቅ የሆነ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት አላማ ከስድስት አመታት በፊት የማጥቃት ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ 10,000 በላይ ሰዎች እንደገደለ ታውቋል።
የዜና ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።