የኬንያ ወታደራዊ ሃይል የሶማልያው ድንፈኛ እስላማዊ ቡድን አል-ሸባብ የስለላ ሀላፊን ገድያለሁ ይላል። ቡድኑ ግን አስተባብሏል።
የኬንያ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ዴቪድ ኦቦንዮ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አብዲራሕማን መሐመድ ዋርሳሜ በመባልም የሚታወቀው ማሃድ ካራቴ ባለፈው ሳምንት ሰኞ በደቡብ ሶማልያ ላይ በተካሄው የአየር ድብደባ ከአስር የመካከለኛ ደረጃ አባላት ጋር ተገድሏል ብለዋል።
አንድ የአል-ሸባብ ደጋፊ ድረ-ገጽ ግን ዘገባው ተሳስቷል ብሏል። ካራቴ ደህና ነው። ሰፈሩ በአየር ድብደባ አልተመታም ይላል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካራቴን ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችል መረጃ ላቀረበ ሰው የ $5 ሚልዮን ዶላር ሽልማት ለመስጠት ቃል ገብቷል። ባለፈው አመት ኬንያ ውስጥ ወደ 150 የሚጠጉ ሰዎች በተገደሉበት በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ጥቃት ካራቴ አብይ ሚና እንደነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።
የኬንያ መንግስት ከአራት አመታት በፊት አል-ሸባብን ለመዋጋት ወታደሮች ወደ ሶማልያ ከላከ ወዲህ ጽንፈኛው ቡድን ኬንያ ውስጥ በርካታ ጥቃቶች ማካሄዱ የሚታወቅ ነው።