የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ዋናው የአል-ሸባብ መሪ አቡ ኡቤይዳ ያለበትን የሚጠቁም መረጃ ለሚሰጥ እስከ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወሮታ እንደሚሸልም አውጁዋል። አቡ ኡቤይዳ የረጅም ጊዜው የቡድኑ መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር በዩናይትድ ስቴትስ ኣብራሪ አልባ ኣውሮፕላን ድሮን ከተገደለ በሁዋላ መሪነቱን የተረከበው ነው። ማሃድ ካራቴ፡ ማአሊም ዳዉድ እና ሃሰን አፍጉዬ የሚባሉ ሌሎች ሶስት ዋና ዋና የአልሸባብ አመራር ኣባላት የሆኑ የሚያስይዝ ጥቆማ ለሚያቀብል ደግሞ የአምስት ሚሊዮን ዶላር ወሮታ ተመድቡዋል።
ካራቴ አብዲራህማን መሃመድ ዋርሳሜ በሚል ስምም የሚታወቀው ካራቴ ባለፈው እ ኤ ኣ ሚያዝያ ሁለት ኬንያ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኣንድ መቶ ኣርባ ስምንት ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት በማቀነባበር ቁልፍ ሚና የተጫወተ ነው ተብሉዋል። ዳዉድ ደግሞ አልሸባብ በሶማሊያ መንግሥትና በምዕራባውያን የቡድኑ ዒላማዎች ላይ የሚያካሄዳቸውን ጥቃቶች መሪ ኣፍጎዬ ለቡድኑ ጥቃቶች ማካሄጃ ገንዘብ ኣሰባባሳቢ መረቦችን የሚቆጠጠረው መሆኑ ተመልክቱዋል።
ማአሊም ሳልማን እና ኣህመድ ኢማን ኣሊ የሚባሉትን ለሚጠቁም ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ እስከሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወሮታ መድባለች። ሳልማን የሌላ የአፍሪካ አካባቢ ባዕዳን ሽብርተኛ ተዋጊዎችን የሚመራ አሊ ደግሞ ኬንያውያን ወጣቶችን ለተዋጊነት የመለመለ ገንዘብም ለቡድኑ ያሰባሰበ ነው ተብሎ ይፈለጋል።
ይህ ኣዲስ ይፋ የተደረገው ወሮታ የተመደበው በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወሮታ ለፍትህ መርሃ ግብር መሆኑ ታውቁዋል።
በመርሃ ግብሩ ድረ ገጽ መረጃ መሰረት እስካሁን በዚህ መርሃ ግብር ዓለም ኣቀፍ የሽብር ጥቃቶችን ለመከላከል ያስቻሉ ወይም ደግሞ በተፈጸሙ ጥቃቶች የሚፈለጉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያደረጉ መረጃዎች ላቀበሉ ከሰማኒያ ለሚበልጡ ሰዎች ኣንድ መቶ ሃያ ኣምስት ሚሊዮን ዶላር ወሮታ ከፍሉዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ሙክታር ሮቦው እና ኣብዱላሂ ያሬ የሚባሉትን ጨምሮ ሊሎች የሚፈለጉ የእልሸባብ መሪዎችን ለሚያሲዝ መረጃ የመደበቸው ወሮታም እንዳለ ነው።