ዋሽንግተን ዲሲ —
በአፍሪቃ ኅብረት ሠራዊት የሚታገዙት የሶማልያ ወታደሮች፣ በታች ሸበሌ ክልል ተምትገኘውንና መርካ የምትባለውን ስትራተጃዊት የወደብ ከተማ ከአል-ሻባብ ይዞታ ማስለቀቃቸውን የዐይን ምስካሪዎችና የመንግሥቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
"ከአፍሪቃ ሕብረት ወታደሮች ጋር በመተባበር ዛሬ ማለዳ ላይ የመርካ ከተማን መልሰን ማርከናል" ሲሉ፣ የክልሉ ገዢ ኢብራሂም አደን አሊ ለቪኦኤ በቴሌፎን ገልጸዋል።
ነውጠኞቹ በሽሽት ላይ ስለነበሩ አንዳችም የመቋቋም ኃይል እንዳላሳዩ የገለጹት የክልሉ ገዢ፣ በአሁኑ ሰዓትም የሕብረቱና የሶማልያ ሠራዊት ከተማይቱን በማጽዳት ላይ እንደሚገኙ አክለው ተናግረዋል።
የሁለቱ የተባበረ ሠራዊት ከተማይቱን ከነውጠኛው ቡድን አል-ሻባብ ነፃ ለማውጣት ታንክና የጦር ተሽከርካሪዎችን እንደተጠቀሙ፣ ምስክርነታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።