በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ ዘገባ ለማቅረብ የተንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ውለው ተለቀቁ


የምስራቅ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ማህበር
የምስራቅ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ማህበር

ሁለት የዓለምአቀፍ ጋዜጠኞች እና አስተርጓሚያቸው በኦሮሚያ ተቃውሞና ድርቅ ዙሪያ ዘገባ ለማቅረብ በተንቀሳቀሱበት ወቅት፤ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው ተመለሱ። ጋዜጠኞቹ ለ24 ሰዓታት ታስረው ተለቀዋል።

በኢትዮጵያ ሁለት ዓለምአቀፍ ጋዜጠኞችና አስተርጓሚያቸው በኦሮሚያ የተከሰተው ድርቅና የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ዘገባ ለማቅረብ ሲንቀሳቀሱ ለ24 ሰዓታት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቁ።

የብሉምበርግ የዜና ምንጭ ዘጋቢ ዊሊያም ዴቪድሰን፣ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የምትዘግበው ጄሲ ፎርትንና አስተርጓሚያቸው በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ያለምንም ማብራሪያ ከአዋሽ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በፌዴራል ፖሊስ ታጅበው እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላ አዳር ታስረው መለቀቃቸውን አስታውቀዋል።

ጋዜጠኞቹ ወደ ኦሮሚያ ክልል ያመሩት ባለፈው ሮብለት ሲሆን፤ ቀዳሚው ቆይታቸው በአዳማ ዩኒቨርስቲ ነበር። በዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን በተለይ በኦሮሚያ የሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችን አስመልክቶ የብሉምበርግ ዘጋቢ ዊሊያም ዴቪድሰንን አነጋግረንው ነበር።

ሐሙስ ጠዋት ተነስተው ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ አመሩ። የጉዟቸው አላማ በምእራብ ሐረርጌ በቅርቡ በአሰቦች ሒርናና ሌሎች ከተሞች የተቀሰቀሱ ሰልፎችን አስምልክቶ ሁኔታውን ለመከታተልና ለመዘገብ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በመጉዳት ላይ ያለው ድርቅ፤ በምእራብ ሀረርጌ ያስክተለውን ጉዳትም ለመመልከትና ለመመዘን እንደሆነ ዊሊያም ዴቪድሰን ያስረዳል።

በአዋሽ ከተማ ምሳ በልተው ከከተማ ወጣ እንዳሉ፣ "ከምሥራቅ ወደ ደቡብ ምሥራቅ እያመራን ሳለ፤ አንድ የፍተሻ ጣቢያን አለፈን ከዚያ በኋላ የፌደራል ፖሊስ መኪና የኛን መኪና አስቆመንና (እኔ የራሴን መኪና ነበር ይዤ የነበር የምጓዘው) ከሌላ የውጭ ጋዜጠኛ እና ከአስተርጓሚ ጋር፣ ፌደራል ፖሊሶች ፓስፖርታችንን፣ የመኖርያ ፍቃዳችንና ዜግነታችንን እንድናሳይ ጠየቁን ።" ይላይ ዊልያም።

ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ የምታቀርበው ጄሲ ፎርትን እና ኢትዮጵያዊ አስተርጓሚያቸው ነበሩ በመኪናው ውስጥ። በወቅቱ ከጸጥታ ባለስልጣኖችም ሆነ ከያዟቸው የፌዴራል ፖሊስ ባልደረቦች ለምን እንደተያዙ በህግም ሆነ በአሰራር ተጠቅሶ የተነገራቸው ምንም አይነት ነገር እንደሌለ ዊሊያም ዴቪድሰን ለቪኦኤ አስረድቷል።

የብሉምበርግ የዜና ምንጭ ዘጋቢ ዊሊያም ዴቪድሰን
የብሉምበርግ የዜና ምንጭ ዘጋቢ ዊሊያም ዴቪድሰን

በአዋሽ የነበራቸው ቆይታ አጭር ነበር በጥቂት ደቂቃዎች ወስጥ፣ "በፖሊስ ታጅበን ወደ አዲስ አበባ እንድንመለስ ተወሰነ። ውሳኔው በ10 ደቂቃ ውስጥ ነው የተወሰደው።" በማለት ገልጾልናል ዊልያም።

በተጨማሪም "ምን እንዳጠፋን የሚገልጽ ምልክት አልነበረም። ምን እንዳጠፋንም ግልጽ አልነበረም። በቀጥታ የምናነጋግራቸው የነበርንው ሰዎች ግን ትእዛዝ እንደተሰጣቸው ብቻ ነው የነገሩን።" ብሏል።

ጄሲ ፎርትን
ጄሲ ፎርትን


ከዊሊያም ዴቪድሰን ጋር የታሰረችው ጄሲ ፎርትን በትዊተር ገጿ፤ “በኢትዮጵያ ዘገባ ሳቀርብ አዳሬን ታስሬ ነበር” በማለት የምስራቅ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ማህበር ያወጣውን መግለጫ አካታለች።

የምስራቅ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ማህበር በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ዙሪያ የሚታዩ ጥሰቶች ክፉኛ እንዳሳሰቡት አስታውቋል። በኢትዮጵያ ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች እንዲሁ በዘፈቀደ ለአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር እየዋሉ፤ ስራቸውን እንዳይሰሩ ሆን ተብሎ ይደረጋል፤ አሰራሩም የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ይጥሳል ብሏል ማህበሩ። ኢልያ ግሪንደርፍ የድርጅቱ የቦርድ ሃላፊ ናቸው።

"ጋዜጠኞችን ማሰር የሚጠቅማቸው አይደለም። አነጋጋሪና ጥንቃቄ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ (ለምሳሌ እንደ ኦሮሚያ ተቃውሞዎች ያሉ) ጋዜጠኞች ዘገባ እንዳያቀርቡ ማስቆም የሚያመጣው ፋይዳ የለም። በጣም የሚያሳስበንና ድምጻችንን እንድናሰማ የሚያስገድደን ሁኔታ አለ። የኢትዮጵያ መንግስት ከለት ወደለት በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚያከናውነውን አፈና እያጠናከረ ሲሄድ ተመልክተናል። በተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ትገኛለች። በአፍሪካ ሁለተኛው ትልቅ የህዝብ ብዛት ወዳላት ሀገር የምጣኔ ሀብቱን እድገት ተከትሎ፤ በስፋት ወደ ኢትዮጵያ ስራ ለመስራት የንግዱ ማህበረሰብ በመትመም ላይ ይገኛል። የሚያድጉ ሀገሮች እንደ ዩናይትድስ ስቴይትስ፣ ብርታንያና አውስትራሊያ የመሳሰሉ አይነት የመብትና የአሰራር ደረጃ መኖር እንዳለበት እናምናለን።" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም። ከፍተኛ የመንግስቱን ባለስልጣናት ለማግነጋገር ሞክረን አልተሳካልንም።

ሔኖክ ሰማእግዜርና ሳሌም ሰለሞን ጉዳዩን ተከታትለው ያቀረቡትን ዘገባ ለማዳመጥ የድምጽ ፋይሉን ይጫኑ።

በኦሮሚያ ዘገባ ለማቅረብ የተንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ውለው ተለቀቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:52 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG