ፍቃዱ የመንግሥቱ ንብረት በሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኦሮሚያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ውስጥ የሚሠራ ሲሆን የተያዘውም ከትናንት በስተያ ቅዳሜ ከቤቱ መሆኑን ዘገባዎችን የጠቀሰው የሲፒጄ መግለጫ አመልክቷል፡፡
ፍቃዱ የተያዘበትና የታሠረበትን ምክንያት ሲፒጄ በውል አለመለየቱን ገልፆ የኦሮሚያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ግን በቅርብ ሣምንታት በክልሉ ውስጥ ከአዲስ አበባና አካባቢዋ የተቀናጀ ልማት ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተነሣውን አለመረጋጋት ሲዘግብ እንደነበረ አስታውሷል፡፡
ከመንግሥትም፣ በውሣኔዎቹ ጫና ሊያድርባቸው ከሚችሉ ወገኖችም የሚወጡ መረጃዎችን ፍሰት ለማረጋገጥ ጋዜጠኞች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሱ ቫለንታይን “ባለሥልጣናቱ ፍቃድ ምርከናን በአፋጣኝ እንዲፈቱ እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡
ፍቃዱ የት እንዳለ ቤተሰቡ እንደማያውቅና ጠበቆችም እንዳላገኙት መግለጫው ጠቁሟል፡፡
የፍቃዱን እሥራት አስመልክቶ ሲፒጄ ላወጣው ጥያቂ ከአዲስ አበባም ሆነ ናይሮቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምላሽ አለማግኘቱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በለንደን የምጣኔ ኃብትና የፖለቲካ ሣይንስ ትምህርት ቤት በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ እየሠሩ ያሉ አወል አሎ የሚባሉ አጥኝ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ አል ጃዚራ ዌብ ሣይት ላይ ያወጡትን ፅሁፍ ሲፒጄ ሲጠቅስ የግንኙነት ጉዳዮች ሚኒስትሩ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ተቃዋሚዎችን “አሸባሪዎች”ና “አጋንንት” እያሉ መጥራታቸውን፤ እንዲህ ዓይነት ቃላት ደግሞ መንግሥቱ ወትሮም ተቃውሞን ለመበተን የሚጠቀምበት እንደሆነ አወል መፃፋቸውን አመልክቷል፡፡
በዚህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሲሦ የሚሆነው የኦሮሞ ሕዝብ በሚኖርበት ክልል ውስጥ የተነሣው ተቃውሞ ቢያንስ ሰላሣ ከተሞችን መንካቱንና አምስት መቶ ሰው ካለፈው ኅዳር መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ መታሠሩን ሲፒጄ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ አሥር ጋዜጠኞችን አሥራ የምትገኝ፣ ጋዜጠኞችን በማሠር በአፍሪካ ሦስተኛዋ ሃገር መሆኗን ሲፒጄ ባለፈው ኅዳር 21/2008 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርቱ ማሳወቁን አስታውሷል፡፡