በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ያለስምምነት በተጠናቀቀው የሕዳሴ ግድብ ድርድር ግብጽ የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላት ተገለጸ


ያለስምምነት በተጠናቀቀው የሕዳሴ ግድብ ድርድር ግብጽ የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላት ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:53 0:00

ያለስምምነት በተጠናቀቀው የሕዳሴ ግድብ ድርድር ግብጽ የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላት ተገለጸ

በዐዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት የተካሔደው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አራተኛው ዙር ድርድር፣ ያለስምምነት እንደተጠናቀቀ፣ ትላንት ያስታወቁት ኢትዮጵያ እና ግብጽ፣ ለውጤት አልባነቱ አንዳቸው ሌላቸውን ወንጅለዋል፡፡

ግብጽ፥ “ውይይቱ ያልተሳካው ኢትዮጵያ ምንም ዐይነት ስምምነት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመኾኗ ነው፤” ስትል፤ ኢትዮጵያም በበኩሏ፣ “የስምምነቱን መንገድ የዘጋችው ግብጽ ናት፤” ብላለች፡፡

በድርቅ ወቅት የሚኖረው የውኃ አያያዝ እና አለቃቀቅ፣ በድርድሩ ከፍተኛ ልዩነት የታየበት ጉዳይ እንደነበረ፣ የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ዶር. ስለሺ በቀለ ገልጸዋል፡፡

ግብጽ፣ “ከዚኽ በኋላ ድርድሩን የመቀጠል ፍላጎት የለኝም፤” እንዳለች የገለጹት አምባሳደር ስለሺ፣ የአፍሪካ ኅብረት ዳግም ወደ አደራዳሪነቱ ሊመለስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን፣ በዐዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ያካሔዱት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር ድርድር፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ያለስምምነት መቋጨቱን ያስታወቁት ኢትዮጵያ እና ግብጽ፣ ለውጤት አልቦነቱ እርስ በርስ ተወነጃጅለዋል፡፡

ያለፉት አራት ዙር ድርድሮች የተካሔዱት፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤል-ሲሲ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት እና አለቃቅ ዓመታዊ ክዋኔ ላይ፣ በአራት ወራት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ እንዲደረስ፣ በ2015 ዓ.ም. ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በተስማሙት መሠረት ነው፡፡

ይኹንና፣ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ሲካሔድ የቆየው የግድቡ ድርድር፣ በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም ላይ ከተቋረጠ በኋላ፣ በሦስቱ የተፋሰሱ ሀገራት መካከል፣ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ፣ በካይሮ እና በዐዲስ አበባ በተደረጉ የአራት ዙር ድርድሮች ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡

ለድርድሮቹ ፍሬያማ አለመኾን፣ ኹለቱ ሀገራት ባወጡት መግለጫ እርስ በርስ ተወቃቅሰዋል፡፡

የግብጽ የውኃ ሀብት እና መስኖ ሚኒስቴር፣ “ውይይቱ ያልተሳካው፥ ኢትዮጵያ ምንም ዐይነት ስምምነት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመኾኗ ነው፤” ሲል ከሷል፡፡

ስምምነት ላይ ላለመደረሱ፣ ግብጽን ተጠያቂ የምታደርገው ኢትዮጵያም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ፣ “ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቧ በመቀጠል፣ ወደ መግባባት የሚወስደውን መንገድ ዘግታለች፤” ስትል ወቅሳለች።

የሦስትዮሽ ድርድሩ ሲካሔድ የነበረው፣ 16 አንቀጾች ባሉት የጋራ መደራደሪያ ሰነድ ላይ በመመሥረት ሲኾን፣ ከፍተኛ ልዩነት የታየውም፣ በድርቅ ወቅት በሚኖረው የውኃ አያያዝ እና አለቃቀቅ ላይ ትኩረት በአደረገው አንቀጽ እንደኾነ፣ የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶር.) ድርድሩን አስመልክተው፣ ዛሬ ረቡዕ፣ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ልናስኬድ የቻልነው እስከ ስድስተኛው ክፍል ነው ነው። ስድስተኛው ክፍል ላይ ደግሞ ልዩነት አለ፡፡ ይሄም የድርቅ ሁኔታን የሚያመላክተው የውሃ አያያዝና አለቃቅ ጉዳይ ነው፡፡”

“ልናስኬድ የቻልነው እስከ ስድስተኛው ክፍል ነው ነው። ስድስተኛው ክፍል ላይ ደግሞ ልዩነት አለ፡፡ ይሄም የድርቅ ሁኔታን የሚያመላክተው የውሃ አያያዝና አለቃቅ ጉዳይ ነው፡፡” ያሉት ዶር. ስለሺ በዚህ ላይ መግባባትና መቀራረብ ስላልተቻለ፣ ስድስት ሰዎች ያሉበት የባለሞያዎች ቡድን ጉዳዩን እንደገና እንዲመለከት ሁለት ሰዎች መወከላቸውን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ የተወከሉት ሰዎች ደግሞ ከሁለቱ ቀናት የሚኒስትሮቹ ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ መወያየታቸውን አምባሳደር ስለሺ ጨምረው አስረድተዋል።

ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅት በሚለቀቀው የውኃ መጠን ላይ፣ በተደራዳሪዎቹ ሀገራት መካከል የቁጥር ልዩነቶች መኖራቸውን፣ አምባሳደር ስለሺ ጠቅሰዋል፡፡ በውኃው የክፍፍል መጠን ላይ ስምምነት በሌለበት ኹኔታ፣ ከታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በተቃራኒ ኢትዮጵያ፣ ቋሚ ቁጥር መቀመጥ የለበትም፤ የሚል አቋም እንዳላት፣ ዋና ተደራዳሪው አብራርተዋል፡፡

“ይሔን ቁጥር ስንሰጥ የኢትዮጵያን የወደፊት የመልማት ዕድል በሚገድብ መልኩ ሳይኾንን፣ የትብብር ስለሆነ ያንን ሊያስተካክል የሚችለው ሁላችንም የውሃ መብት ክፍፍላችን ሲታወቅ በዛ ስሜት እንሠራ።አን። እስከዛው መረጃ እየተለዋወጥን መቀጠል አለብን የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ ይሔ ደግሞ ፍትሐዊነት ነው፡፡ ሕዳሴ ግድብን ብቻ ስለሠራን ልማት አናቆምም፡፡ ከላይ የምንሠራቸው ግድቦች የውሃ ጉዳይ በኛ ድርሻ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ አሁን ያ ድርሻ የተቀመጠ ስላልሆነ በድርድር ውስጥ ለዚህ ዓይነት ችግር አጋልጦናል” ያሉት አምባሳደር ስለሺ ኢትዮጵያ፣ “ግትር አቋም ይዛለች፤” በሚል ግብጽ የምታቀርበውን ውንጀላም አስተባብለዋል፡፡

“ድርቅ ቢከሰት፣ ተፈጥሮ ከምትሰጠው በላይ ውሃ ጨምሮ ከመስጠት ሌላ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ከዛ በላይ መፍትሔ የለም፤ ቢኖር እነሱም ያቀርቡት ነበር፡፡” ያሉት ዋና ተደራዳሪው፤ “የሚፈለገውን መፍትሔ አስቀምጠናል፡፡ ነገር ግን እኛ ሀገር ላይ ጉዳት በሚያስከትል፣ ወይም ቀደም ሲል አለን በሚሉት የውሃ ኮታ መሰረት፣ ውሃውን ሙሉ በሙሉ ከተካፈሉ በኋላ ኢትዮጵያ ይሄን አረጋግጣ እንድትሰጣቸው የመፈለግ አካሔድ የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ ትክክለኛም አይደለም፤ እኛ ሀገር ሊያሰቅል ይችላል፡፡ የትም ሀገር ቢሆን ሃብቱን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ አይሰጥም፡፡ እንደላይኛው ተፋሰስ እኛ ብቻችንን እንጠቀም አላልንም፡፡ ተካፍለን አብረን እንልማ የሚል አቋም ነው ያለን፡፡” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በድርድር ሽፋን፣ በኣባይ ወንዝ ላይ ከቁጥጥር ውጭ የኾነ ባለቤትነት እንዳላት፣ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ይኹንታ ለማግኘት ብቻ መደራደርን መርጣለች፤” ያለው የግብጽ የውኃ ሀብት እና መስኖ ሚኒስቴር፣ “ግብጽ በዓለም አቀፍ ቻርተሮች እና ስምምነቶች መሠረት፣ በውኃዋ እና ብሔራዊ ደኅንነቷ ላይ ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ጥቅሟን የመከላከል መብቷ የተጠበቀ ነው፤” ሲልም አስጠንቅቋል፡፡

“ኢትዮጵያ በድርድር ሽፋን፣ በኣባይ ወንዝ ላይ ከቁጥጥር ውጭ የኾነ ባለቤትነት እንዳላት፣ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ይኹንታ ለማግኘት ብቻ መደራደርን መርጣለች፤”

ኢትዮጵያ በበኩሏ፣ በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር፣ በሦስቱ ሀገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር ያለመ እንጂ፣ “በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ የኢትዮጵያን መብቶች ለማስነጠቅ አይደለም፤” ብሏል። የግብጽ መግለጫ፣ “የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር እና የአፍሪካ ኅብረትን ድንጋጌ የሚፃረር” እንደኾነም ሚኒስቴሩ ተችቷል፡፡ ኢትዮጵያ፣ የውኃ ሀብቷን፥ “ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በኾነ መንገድ፣ የአኹንና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት መጠቀሟን ትቀጥላለች፤” ሲልም አክሏል፡፡

አምባሳደር ስለሺ በቀለ በዛሬው መግለጫቸው፣ በድርድሩ ላይ ግብጽ፣ “ነባሩን የቅኝ ግዛት ዘመን የውኃ ክፍፍል የሚያንጸባርቅ” ሐሳብ በተደጋጋሚ ከማንሣቷም በላይ፣ “ቀጣይ ድርድር የማድረግ ፍላጎት እንደሌላትም ይፋ አድርጋለች፤” ብለዋል፡፡ ይኹንና ቀጣይ የድርድሩ ሒደት፣ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ መጠን፣ ከ94 በመቶ በላይ መድረሱን የገለጹት ዋና ተደራዳሪው አምባሳደር ስለሺ በቀለ(ዶር.)፣ ተጨማሪ አምስት ተርባይኖችም፣ በዚኽ ዓመት ኀይል ማመንጨት ይጀምራሉ፤ ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG