በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኅዳሴ ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገፅ ላይ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገፅ ላይ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ

የጸጥታው ምክር ቤት እንዲሰበሰብ የአረብ ሊግ፣ የግብጽ እና የሱዳንን ጥያቄ በማንገብ፣ የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል ቱኒዚያ ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት ምክር ቤቱ ትናንት ባደረገው ስብሰባ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን ድርድር ደግፏል፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ ግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ለጸጥታው ምክር ቤት ስጋትና ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን የኅዳሴ ግድብ ለግብጽ የሕልውና ስጋት እንደሆነ ለምክር ቤቱ የገለጹት የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ፣ ግብጽ ይህን እንደማትታገስ እና የጸጥታው ምክር ቤትም እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

ከግብጽ ጋር ተመሳሳይ አቋም የምታራምደው ሱዳንም እንዲሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማሪያም አል ሳዲቅ አል ማህዲ በኩል ባስተላለፈችው መልዕክት ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ያለ ስምምነት ግድቡን እንዳትሞላ ያግዳት ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ/የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገፅ ላይ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ
የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ/የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገፅ ላይ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ

የዓባይ ወይም የናይል ወንዝ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት መሆኑንም የገለጹት የኢትዮጵያው ተወካይ የተገኙት የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የሱዳንና የግብጽ ፍላጎት ከግድቡ ጋር የተያያዠ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውሃውን እንዳትጠቀም ማድረግእንደሆነ አብራርተው፣ ኢትዮጵያ ብትፈልግ እንኳን የዓባይን ውሃ አለመጠቀም እንደማትችል አንስተዋል፡፡

ወትሮውን የተለያየ አቋም በማንጸባረቅ የሚታወቁትን አሜሪካና ሩሲያን ጨምሮ ሁሉም የምክር ቤቱ ቋሚና ተለዋጭ አባላትም በኅዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው ልዩነት በአፍሪካ ሕብረት መሪነት በሚካሔደው ድርድር እንዲፈታ አሳስበዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ሰላምና ጸጥታ በአፍሪካ በሚል ርዕስ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ፣ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ትናንት ሐምሌ 1/2013 ዓ.ም ሌሊት ላይ ስብሰባ አድርጓል፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት በትግራይ ክልል ጉዳይ የተሰበሰበው ምክር ቤቱ፣ ትናንትያደረገው ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው ነው፡፡

የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ በጸጥታው ምክር ቤት እንዲታይ የአረብ ሊግ፣ የግብጽ እና የሱዳንን ጥያቄ በማንገብ፣ የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል ቱኒዚያ ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት ነው ምክር ቤቱ ስብሰባ የተቀመጠው፡፡

ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመሯ ይፋ ከተደረገ ከቀናት በኋላ በተካሔደው በዚህ ስብሰባ ላይ ግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀው ለጸጥታው ምክር ቤት ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

የኅዳሴ ግድብ ለግብጽ የሕልውና ስጋት እንደሆነ ለምክር ቤቱ የገለጹት የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ፣ ግድቡ ግብጽ የምታገኘውን የውሃ መጠን በመቀነስ ሃገሪቱን ለተለያዩ ችግሮች እንደሚዳርግ በማብራራት፣ ግብጽ ይህን አትታገስም ብለዋል፡፡ የጸጥታው ምክር ቤትም ግድቡ ለግብጽ የሕልውና ስጋት እንዳይሆን ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ/የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገፅ ላይ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ/የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገፅ ላይ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ

“የሕዳሴ ግድብ በግብጽ ላይ የተለያዪ የውሃ እጥረቶችን ያስከትላል፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃን ይቀንሳል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የመስኖ ውሃ እንዳያገኙ ሊያደርግ ይችላል፤ በሺዎች ሄክታሮች የሚቆጠሩ የእርሻ መሬቶችን ያወድማል፣ በረሃማነትን ያስፋፋል ሥነ ምህዳራዊ ሥርዓትንም ይጎዳል፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችም ተጋላጭነትን ይጨምራል።ይህ ግብጽ ልትታገሰው የማትችለው እና የማትታገሰው ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ በጸጥታው ምክር ቤት በኩል ይህን ክስተት የመከላከል እና ግድቡ ለግብጽ የሕልውና ስጋት እንዳይሆን የተቻለውን ሁሉ ማድረግየግድ ያስፈልገዋል፡፡”

ሦስቱ ሀገራት በስድስት ወራት ውስጥ አስገዳጅ (አሳሪ) ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እና ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት እንድታቆም የሚጠይቀውን በቱኒዚያ የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያጸድቅም የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጠይቀዋል፡፡

ከግብጽ ጋር ተመሳሳይ አቋም የምታራምደው ሱዳንም እንዲሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማሪያም አል ሳዲቅ አል ማህዲ በኩል ባስተላለፈችው መልዕክት ግድቡ ለሱዳንም ስጋት መሆኑን አንስታለች፡፡ በተለይ ከሕዳሴው ግድብ በታች የሚገኘው የሮሳሪየስ ግድብ አደጋ እንደተደቀነበት እናበሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናው ያንም የግብርና ሥራቸው እንደሚስተጓጎል የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ያለስምምነት ግድቡን እንዳትሞላ ያግዳት ዘንድ ጠይቀዋል፡፡

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ሳዲቅ አል ማህዲ /የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገፅ ላይ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል ሳዲቅ አል ማህዲ /የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገፅ ላይ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ

“ምክር ቤቱ ቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታን በማረጋገጥ ረገድ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚካሔደው ድርድር እንዲቀጥል በማድረግ፣ በሕብረቱ ጥላ ስር ተደራዳሪዎች ድርድራቸውን እንዲጀምሩ በማድረግ፣ ከስምምነት ላይ እንዲደረስ ዓለማቀፍ አደራዳሪዎች እና ታዛቢዎች ድርድሩን እንዲያስኬዱ በማድረግ፣ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሱዳናውያን ላይ ስጋት ከሚደቅን ከማንኛውም የተናጥል እርምጃ እንድትታቀብ በማድረግ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡” ብለዋል።

ኢትዮጵያን በመወከል ንግግር ያደረጉት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣ በግድብ ጉዳይ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ሲቀመጥ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሰው፣ የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በምክር ቤቱ መታየቱን በጽኑ አውግዘዋል፡፡ የግድቡ ሁለተኛ ሙሌት በ2015ቱ የመርሆች ስምምነት መሰረት የሚካሔድ እና የግድቡ የግንባታ አካል መሆኑንም ዶ/ር ስለሺ ገልጸዋል፡፡

የዓባይ ወይም የናይል ወንዝ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት መሆኑንም የገለጹት ዶ/ር ስለሺ የሱዳንና የግብጽ ፍላጎት ከግድቡ ጋር የተያያዠ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውሃውን እንዳትጠቀም ማድረግ እንደሆነ አብራርተው፣ ኢትዮጵያ ብትፈልግ እንኳን የዓባይን ውሃ አለመጠቀም እንደማትችልአንስተዋል፡፡

ዶ/ር ስለሺ ስለዚሁ ሲያስረዱ፤ “የጎረቤቶቻችንን ስጋት ለመቅረፍ በጥሩ እምነት ተደጋጋሚ ጥረት ካደረግን በኋላ ተቃውሞአቸው በግድቡ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን ኢትዮጵያ ምንም ውሃ እንዳትጠቀም ማድረግ እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ተገደናል፡፡ እውነታው ግን እኛ ሌላ አዋጭ አማራጭየሌለን መሆኑ ነው፡፡ እንደግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ በቂ የከርሰምድር ውሃ የላትም፤ የባሕር ውሃም የለንም፣ 70 በመቶ የሚሆነው የኔ ሀገር ውሃ በናይል ተፋሰስ የሚገኝ ነው፡፡

ብንፈልግ እና ብንሞክር እንኳን ናይልን አለመጠቀም አንችልም፡፡ ኢትዮጵያውያን የናይል ወንዝን መጠቀም ይችላሉ ወይስአይችሉም የሚለውን የጸጥታው ም/ቤት መመለስ ይጠበቅበታል፡፡ በኢትዮጵያውያን ስም ይሕን ምክር ቤት እና ዓለማቀፉን ማህበረሰብ፣ ኢትዮጵያውያን ከናይል መጠጣት ይችላሉን የሚለውን እንዲመልሱ እጠይቃለሁ፡፡ ማናችንም ሌሎች ሲጠጡ እየተጠማን መቀጠል የለብንም፡፡” ብለዋል።

በመሆኑም ም/ቤቱ የግድቡን ጉዳይ መመልከት የለበትም ያሉት ዶ/ር ስለሺ፣ ይህ ስብሰባ የጸጥታው ምክር ቤት በግድቡ ጉዳይ የሚያደርገው የመጨረሻው ስብሰባ እንዲሆን እና ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመልስ ጠይቀዋል፡፡

ወትሮውን የተለያየ አቋም በማንጸባረቅ የሚታወቁትን አሜሪካና ሩሲያን ጨምሮ ሁሉም የምክር ቤቱ ቋሚና ተለዋጭ አባላትም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው ልዩነት በአፍሪካ ሕብረት መሪነት በሚካሔደው ድርድር እንዲፈታ አሳስበዋል፡፡

በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚደረገው ድርድር በአስቸኳይ እንዲቀጥል የጠየቁት በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ፣ ተደራዳሪ ሀገራት ሂደቱን ከሚጎዳ እርምጃ እንዲታቀቡም ጠይቀዋል፡፡

“የግብጽ እና የሱዳን የውሃ ደህንነት እና የግድቡ አስተዳደር እና ደህንነት ስጋት ከኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት ጋር መታረቅ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚጀምረው ውጤታማ እና ተጨባጭ ድርድሮችን በማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ድርድሮች በአፍሪካ ሕብረት መሪነት መካሔድ እና በአስቸኳይ መጀመር አለባቸው፡፡ ይህሂደት በ2015 በተደራዳሪዎች የተፈረመውን የመርሆች ስምምነት መጠቀም አለበት፡፡ ይህን አለመግባባት ለመፍታት የአፍሪካ ሕብረት ትክክለኛው ቦታ መሆኑን እናምናለን፡፡ ውጤታማ ስምምነት ላይ ለመድረስ አሜሪካ ፖለቲካዊ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነች፡፡”

ኢትዮጵያ ባትቀበልም ግብጽ እና ሱዳን ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ ተመድ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረትም በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ አለመግባባቶችን ለመፍታት ግብጽ የኃይል እርምጃ ልትወስድ እንደምትችልም መግለጿ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ከአፍሪካ ሕብረትውጭ አደራዳሪዎችን ማብዛት ፋይዳ እንደሌለው የገለጹት በተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ ኃይል ስለመጠቀም የሚሰጡ መግለጫዎችም እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡

“የቴክኒክ እና የሕግ ባለሙያዎቹን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት በግድቡ ላይ ያለውን ልዩነት ለመፍታት የሚያደርገውን ተሳትፎ እናደንቃለን፡፡ ይህ አህጉራዊ ድርጅት የውሃውን ችግር የመፍታት አቅሙ ገና አልተሟጠጠም ብለን እናምናለን፡፡ በኮንጎ ሊቀመንበርነት የሚመራው ህብረቱ በዚህ መንገድጥረቱን እንዲያጠናክር እንጠይቃለን፡፡ በድርድሩ ላይ አደራዳሪዎችን እና ታዛቢዎችን ማብዛት ውጤት አያመጣም፡፡ ይሁንና በተደራዳሪዎቹ ፍላጎት ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ችግሩን ለመፍታት ኃይልን ስለመጠቀም የሚገልጹ መግለጫዎች መቆም እና መከልከል አለባቸው፡፡”

ምንም እንኳን ቱኒዚያ ባቀረበችው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ላይ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ሁሉም የጸጥታው ምክር ቤት አባላት በአፍሪካ ሕብረት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል አሳስበው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

(ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ የተያያዘውን ፋይል ይጫኑ)


XS
SM
MD
LG