በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቆይታ ከ"ዓባይ ዕውነታዎች" ጸሐፊው ዶ/ር ደረጀ በፍቃዱ ጋር


ቆይታ ከ"ዓባይ ዕውነታዎች" ጸሐፊው ዶ/ር ደረጀ በፍቃዱ ጋር
please wait

No media source currently available

0:00 0:31:11 0:00

የዓባይ እውነታዎች

በዓባይ ወንዝ ዙሪያ የተከናወኑ ታሪካዊ ክስተቶችን፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ግፊቶችን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እና ሳይንሳዊ ሁነቶችን የሚዳስስ ጥናታዊ መፅሃፍ ባለፈው ሳምንት እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ጆርጅ ታውን ዩንቨርስቲ ተመርቋል።

ይህን 'How this Happened - Demystifying the Nile', ወይም በአማርኛው 'የዓባይ እውነታዎች' የተሰኘውን መፅሃፍ የፃፉት፣ በጆርጅታውን ዩንቨርስቲ መምህር እና አጥኚ የሆኑት ዶክተር ደረጀ በፍቃዱ ተሰማ ሲሆኑ፣ ከአንደኛው ክፍለዘመን አንስቶ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ከተከናወኑ እና የአህጉሩን ታሪክ ከቀየሩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ክስተቶች በተጨማሪ ከአባይ ወንዝ መነሻ እስከ መዳረሻው በሚገኙ ሀገራት ተጉዘው የሰበሰቧቸውን የግል ምልከታዎችም በመፅሃፉ አካተዋል።

ዶር. ደረጀ፣ በ526 ገጾች በተቀነበበው መጽሐፋቸው፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሳያገኙ፣ በኩራዝ በአደጉበት በአምቦ ከተማ ካሳለፉት ሕይወት ተነሥተው፣ ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንሥቶ፣ የኑቢያ፣ የግብፅ እና የኢትዮጵያ ነገሥታት፣ በዓባይ ዙሪያ የነበራቸውን ግንኙነት፤ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ጨምሮ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታሪክ የቀየሩ ዓለም አቀፍ ክሥተቶችን፣ በዓባይ ዙሪያ የተደረጉ ድርድሮችን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ሳይንሳዊ ሒደቶችን ዳስሰዋል። በመጽሐፉ ምረቃ ላይ በአደረጉት ንግግር፣ የሕዳሴ ግድብ፥ ዛሬም በጨለማ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተስፋ መኾኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ በጣም እንደሚያስፈልግ ጸሐፊው ገልጸው፣ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅና የኤሌክትሪክ ብርሃን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲዳረስ ማድረግ፣ አገሪቱን የሚያዘምን መሠረታዊ ርምጃ ነው፤ በሚል ብዙዎች የሚሟገቱለት አቋም እንደኾነ አስረድተዋል። “የሕዳሴ ግድቡን በጎበኘኹበት ወቅት፣ ከአሰብኹት በላይ የገዘፈ መኾኑ አስገርሞኛል፤” ሲሉ አድናቆታቸውን ያክላሉ፡፡

የሕዳሴ ግድቡን በጎበኘኹበት ወቅት፣ ከአሰብኹት በላይ የገዘፈ መኾኑ አስገርሞኛል፤”

ዶር. ደረጀ፣ በመጽሐፋቸው መጨረሻ ያካተቱትን የግል ምልከታ ለመጻፍ፣ የጥቁር እና ነጭ ዓባይ መነሻ ከኾኑት ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ተነሥተው እስከ መዳረሻው የሜዲትራኒያን ባሕር ድረስ ተጉዘዋል። በጉዟቸው ባለፉባቸው ሀገራት የሚኖሩ ሕዝቦች፣ ከዓባይ ጋራ ያላቸውን ቁርኝትም መዝግበዋል።

“የዓባይ እውነታዎች” መጽሐፍ፥ በሌሎች ባለሞያዎች፣ ስለ ዓባይ የተጻፉ ታሪኮችን ከመያዙም በተጨማሪ፣ በመጨረሻው ምዕራፉ፣ በየሀገሩ ከሚኖሩ ሕዝቦች እና አስጎብኚዎች ጸሐፊው ያዩትንና የሰሙትን አካትቷል። እነዚያን በአካል ተገኝተው የጎበኟቸውን ሰባት ሥፍራዎች ሲዘረዝሩም፤ የጥቁር ዓባይ ምንጭ የኾነውና ከጣና በስተደቡብ 164 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ሰከላ ወረዳ የሚገኘው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ፣ የጣና ሐይቅ፣ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ዩጋንዳ ውስጥ የሚገኘው ጂንጃ የተሰኘ የነጭ ዓባይ መነሻ ሥፍራ፣ አልሞግራንድ የተሰኘው ሁለቱ ዓባዮች ካርቱም ውስጥ የሚገናኙበት ሥፍራ፣ ካይሮ፣ አሌክሳንደሪያ እና በመጨረሻ ዓባይ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር የሚገባበት ቦታ እንደኾኑ አስፍረዋል፡፡

“የዓባይ እውነታዎች” መጽሐፍ፣ ከታሪካዊ ኹነቶች ባሻገር፣ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ የሚታየውን ኢፍትሐዊ አጠቃቀምና በቅኝ ግዛት ወቅት እንግሊዝ ከነበራት ጣልቃ ገብነት አንሥቶ እስከ አሁን የሚታዩ ዓለም አቀፍ ተጽእኖዎችን አጉልቶ ያሳያል።

XS
SM
MD
LG