ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምሮን ካሌ ላሉት ባለስልጣኖች ተጨማሪ $24 ሚልዮን ዶላር እንደሚሰጡ ያስታወቁት ስደተኞቹ ጃንግል በተባለው ደሳሳ ሰፈር ቤቶችን ከሚያፈርሱ ቡድኖች ጋር በተጋጩበት ወቅት ነው።
“ገንዘቡ ሰዎቹን ካሌ ላይ ከሚገኙት ሰፈሮች ወደ ሌሎች የፈንሳይ ቦታዎች ለማዛወር ለሚደረገው ጥረት ይረዳል። ጥገኝነት የማያስፈልጋቸው መጤዎችን መልሰን ወደ ሀገራቸው ለመላካም በኅብረት እንሰራለን።”ብለዋል።
ካምሮን ይህን ያሉት በሰሜን ፈረንሳይ ከፕረዚዳንት ፍራንስዋ ሆላንድ ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ነው። አሁንም ወደ አውሮፓ በመጉረፍ ላይ ያሉት በብዙ ሺህ የሚቆጣሩ ስደተኞች አይያዝ ጉዳይ በአውሮፓ ሀገሮች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል እየተባባሰ ሄዷል።
የአውሮፓ ካውንስል ፕረዚዳንት ዶናልድ ታስክ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የሚፈልሱት ሰዎች አውሮፓ መግባት እንዳይሞክሩ መክረዋል።
ካሌ ያሉት የፈረንሳይ ባለስልጣኖች መጤዎቹን ከጃንግል ወደ ሌሎች ቦታዎች አዛውረው እያሰፈሩ ነው። ብዙዎቹ ካለፍላጎታቸው እንደሚወሰዱ ተዘግቧል። ባለስልጣኖች ስደተኞቹን የሚያሰፍሯቸው የተሻለ ንጽህናና የተሻለ አቅርቦታ ባላቸው እንዲሁም ሰብአዊ ክብራቸው በሚጠበቅባቸው ቦታዎች ነው ይላሉ።
ብሪታንያ ቤተሰብ የሌላቸው ለአካለ-መጠን ያልደርሱ ልጆችን እንደምትቀበል ካምሮን ያስታወቁ ቢሆንም ጃንግል ያሉት ስደተኞች ወደ ብሪታንያ እንዳያመሩ ታግደዋል። በካሌስ ያለው ሁኔታ ሁለቱን ሀገሮች ሲያቃቅር ቆይቷል። የፈረንሳይ የኢኮኖሚ ሚኒስተ ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ከወጣች በካሊስ የሚደረገው የድንበር ቁጥጥር ሊቀር ይችላል ማለታቸው ራሱ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ውጥረት አባብሷል።
የፈረንሳዩ ፕረዚዳንት የኢኮኖሚ ሚንስትሩን ማስጠንቀቅያ ባያስተጋቡም ብሪታንያ በአውሮፓ ህብረት አባልነት እንድትቀጥል ወይም እንድትወጣ በመጪው ሰኔ ወር በሚደረገው ህዝበ-ውሳኔ መራጮች መውጣትን ከመረጡ የፋይናንስና ሌሎች አንደምታዎች መከታላቸው አይቀርም ሲሉ ነው ያስገነዘቡት። ሊዛ ብራያንት ከፓሪስ የላከችውን ዘገባ አዳነች ፍሰሀየ ታቀርበዋለች።