በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወድቆ ከተከሰከው የበረራ ቁጥር 804 የግብፁ አሮፕላን አንዳንድ ስብርባሪዎች እንደተገኙ ግብፅ አስታወቀች


ባለፈው ረቡዕ ሜዲትሬንያን ባሕር ውስጥ ወድቆ ከተከሰከው የበረራ ቁጥር 804 የግብፁ አሮፕላን፣ አንዳንድ ስብርባሪዎች እንደተገኙ፣ ግብፅ አስታወቀች።

የግብፁ ጦር ዋና አዛዥ ብርጌዲየር ጅነራል ሞሃመድ ሳሚርሰኢድ በዛሬው ዕለት በፌስ ቡክ ላይ ባሰፈሩት ቃል፣ ከመንገደኞቹ የግል ንብረቶች መካከል አንዳንድ ነገሮች እንደተገኙና የአርፕላኑ ስብርባሪዎችም ባሕሩ ላይ ተንሳፈው መታየታቸውን አመልክተዋል።

አሮፕላኑ ከራዳር እይታ ከተሰወረበት አካባቢ ጥቂት ፈቀቅ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ደግሞ፤ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች፣ ወንበሮችና ሻንጣዎች መገኘታቸውን የአቴንስ-ግሪክ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

66 ሰዎችን አሳፍሮ ከፓሪስ ወደ ግብፅ ያመራ ከነበረውና ሜዲትሬንያን ባሕር ውስጥ ከተከሰከሰው አሮፕላን በሕይወት የተረፈ አለመኖሩ ቢታወቅም፣ በአሁኑ ሰዓት የሚካሄደው አሰሳና አስከሬን ፍለጋ ግን እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል።

ለአሮፕላኑ መውደቅ፤ ምክንያቱ እስካሁንም በውል አልታወቀም። በምርመራው ለመራዳት በሚል በዛሬው ቀን ሦስት የፈረንሳይ መርማሪዎች ካይሮ ገብተዋል።

ግብፅ ለምታካሂደው ምርመራ ይረዳ ዘንድ እገዛ እንደሚሰጥ የተናገሩት የዩናይትድ ስቴትሱ ውጪ ጉዳይ ጆን ኬሪ ለግጹ አቻቸው ሳመህ ሾክሪ ቃል እንደገቡት፣ ምርመራው እስከሚጠናቀቅ ዩናይትድ ስቴትስ በቅርብ ሆና ትከታተላለች፣ አስፈላጊውን እርዳታም ታደርጋለች።

በአውሮፕላኑ ፍለጋ ከራሷ ከግብፅ ሌላ ፈረንሳይ፣ ዩናይት ስቴትስና ግሪክ አሳሽ አሮፕላኖችና የባሕር መርከቦችን አሰማርተዋል። ለአሮፕላኑ መከስከስ ምክንያቱ "ሽብርተኛነት ነው" ተብሎ በሰፊው የተሰራጨውን አስተያየት በተለይም የፈረንሳይ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አይቀበሉትም።

የግብጹ አቪየሽን ሚኒስትር ሸሪፍ ፋቲ በበኩላቸው፣ ለአደጋው፣ ከቴክኒካዊ ብልሽት የበለጠ፣ "ሽብርተኛነት የጎላውን ቦታ ይይዛል" ይሉና፣ "አደጋው የደረሰው በሆነ ተንኮል ወይም አሻጥር መሆኑ ከተረጋገጠ፣ ይሄ አውሮፕላን የተነሳው ከግብፅ ሳይሆን ከፈረንሳይ መሆኑም ሊጤን ይገባዋል" ብለዋል።

አንዳንድ የአቪዬሽን ጠበብት፣ ለአደጋው መንሥዔ መላ-ምት ከመስጠት መቆጠብ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ "አንድ አሮፕላን ከፍታውን እየጨመረ በሚሄድበት ጊዜ፣ የቴክኒክ ስህተት የመድረሱ ዕድል የመነመነ መሆኑን፣ ያ የሚያጋጥመው ግን አሮፕላኑ ሲነሳ ወይም ሲያርፍ መሆኑን የሚናገሩም" አሉ።

ለማንኛውም እስካሁን ለአደጋው "ተጠያቂ ነኝ" ያለ ወገን አልተሰማም። ለሟቾች፣ ዛሬ ዐርብ በካይሮው ሱልጣን ሁሴን መስጂድ፣ ፀሎትና ተምሳሌታዊ የቀብር ሥነ-ሥርዓት መከናወኑ ታውቋል።

ወድቆ ከተከሰከው የበረራ ቁጥር 804 የግብፁ አሮፕላን አንዳንድ ስብርባሪዎች እንደተገኙ ግብፅ አስታወቀች
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:14 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG