በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቦረና ዝናሙ ቢጀምርም ሰብአዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥ የድርቅ ተፈናቃዮች ጠየቁ


በቦረና ዝናሙ ቢጀምርም ሰብአዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥ የድርቅ ተፈናቃዮች ጠየቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:18 0:00

በቦረና ዝናሙ ቢጀምርም ሰብአዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥ የድርቅ ተፈናቃዮች ጠየቁ

በቦረና ዞን፣ በቅርቡ ዝናም መጣል መጀመሩን ተከትሎ ሲደረግላቸው የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ መቋረጡን የገለጹ የድርቅ ተፈናቃዮች፣ አሁንም ያሉበት አኗኗር ከችግር የማያወጣቸው በመኾኑ፣ ሰብአዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥባቸው ጠየቁ፡፡

ዱብሉቅ በተባለው የመጠለያ ማዕከል የሚገኙት ተፈናቃዮቹ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲደረግላቸው የሰነበተው ሰብአዊ ድጋፍ፣ ብዙዎችን ከሞት መታደጉን ጠቅሰው፣ ነገር ግን፣ በቅርቡ የዝናሙን መጣል ተከትሎ፣ የድጋፍ መጠኑ መቀነሱን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የቦረና ዞን የአደጋ ስጋት አመራር ጽሕፈት ቤት፣ አሁንም በዞኑ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የምግብ ርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸውን አስታውቆ፣ ወደፊት ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን መንገድ ለማበጀት፣ ዐዲስ ዕቅድ አውጥቶ ለክልሉ መንግሥት ማስረከቡንና ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደኾነ አመልክቷል።

ከዱብሉቅ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የመጠለያ ማዕከል፣ በቦረና ዞን ትልቁ የድርቅ ተፈናቃዮች መንደር ነው። የወረዳው አስተዳደር ሓላፊዎች ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በዱብሉቅ ወረዳ ብቻ፣ ከስምንት ሺሕ በላይ አባወራዎች ይገኛሉ። የሰባት ልጆች እናት የኾነችው ወይዘሮ ጅሎ ጉራቻ፣ በዚኽ መንደር መኖር ከጀመረች ሁለት ዓመታትን አሳልፋለች።

መጣል ከጀመረው ዝናም የምናገኘው ውኃ ነው፡፡ በዚኽ ፍጥነት መፍትሔ የሚያመጣልን ሌላ ምን አለ? እኛ አርብቶ አደሮች አደሮች ነን፡፡ የነበረችንን አነስተኛ የእርሻ መሬት ትተን ኮብልለናል። ከተረጂነት የሚያላቅቀን ዝናም አሁን መጣል ቢጀምርም፣ ምንም ሳንሠራበት አለፈን፡፡ በፊት ሲደረግልን የነበረው ድጋፍም ተቋርጧል፡፡ በመጠለያው የሚኖሩት ተፈናቃዮች፣ የምንበላው የለንም፤ እያሉ በጣም ሲጨነቁ አያለኹ፤ አሁን ያለው ኑሮ አስከፊ ኾኗል።

የሦስት ልጆች እናት የኾነችው ጅሎ ሞሉም፣ በእዚኹ መጠለያ ነዋሪ ነች፤ "ዝናሙ ዘንቦ ሣሩ በቅሏል፡፡ ሰዉ እንግዲህ እንደ እንስሳ ሣሩን አይግጥም፡፡ ዝናሙ እንደ ዘነመ፣ ለምን እንደኾነ ባላውቅም ሰብአዊ ድጋፉ ተቋርጧል፡፡ አሁን ከፀሐዩ ቃጠሎ ብቻ ነው ዕረፍት ያገኘነው።"

ባለፉት ወራት፣ በፌዴራሉ መንግሥት ጥሪ መሠረት፣ በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በሚል የድጋፍ ማሰባሰብ መርሐ ግብር በስፋት ሲከናወን እንደነበረ ይታወሳል። ብዙ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ግለሰቦች በየፊናቸው፣ ለዞኑ የድርቅ ተጠቂዎች ያሰባሰቡትን ድጋፍ ሲያደርሱ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት የርዳታ ማሰባሰቡ ቢቀዛቀዝም፣ በዚያን ጊዜ በተደረገው ድጋፍ፣ ብዙ ችግረኞችን በሕይወት ማቆየት መቻሉን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። አብዱበ አሬሮ፣ የዱብሉቅ ከተማ ነዋሪ ነው።

ከዚኽ ቀደም፣ በገንዘብ እና በዐይነት የተደረገው ድጋፍ፣ ችግረኛውን ሕዝብ በእጅጉ ረድቷል፡፡ በወረዳችን የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች፣ በዚኽ የሰብአዊ ተራድኦ ጥሪ ምክንያት ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ ላለፉት ስድስት ወራትም፣ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ድጋፍ አድርገዋል።

“በአሁኑ ወቅት ያለንበት አኗኗር፣ የሰው እጅ ከማየት የሚያወጣን አይደለም፤ ለወደፊት ሕይወታችንም ስጋት አለብን፤” ያሉት ተፈናቃዮቹ፣ ሲደረግላቸው የቆየው ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይቋረጥባቸው ተማፅነዋል፡፡ የዱብሉቅ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የኾኑት አቶ አብዱልቃድር ዓሊ፣ በዞኑ ከስምንት ሺሕ በላይ ተፈናቃይ አባወራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በድርቁ ጊዜ፣ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች፣ ለዞናችን ችግረኞች ድጋፍ አሰባሰበው ደርሰውልናል። በዚኽም የተነሣ፣ በድርቁ የተጠቃው ነዋሪ፣ በረኀብ ከመሞት ተርፎ ለዚኽ የዝናም ወቅት በቅቷል። አሁን ዝናሙ ዘንቦ፣ የተሻለ መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን፣ ዝናም ዘነመ ማለት ችግሩ የለም ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ትልቁ ጥያቄአችን፣ ሙሉ ንብረቱን በድርቁ ያጣውን ማኅበረሰብ እንዴት በዘለቄታው እናቋቁም? የሚለው ነገር ነው፡፡

ዛሬም፣ በጤና እና ሌሎችም መሠረታዊ ሰብአዊ ፍላጎቶች በዞኑ እጥረት መኖሩን አቶ አብዱልቃድር አመልክተዋል። የቦረና ዞን የአደጋ ስጋት አመራር ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ሊበን ሣራ መልሴ፣ መንግሥት በዞኑ ለሚገኙ ከ840ሺሕ በላይ ለሚደርሱ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ በቋሚነት እየሰጠ መኾኑን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። ለተፈናቃዮቹ በቀጣይነት መደረግ ያለበትን ድጋፍ አስመልክተው ሲናገሩም፤

በፊት፣ወገን ለወገን” ተብሎ ይደርስ የነበረው ድጋፍ አሁን ተቋርጧል፡፡ ኾኖም ሕዝባችን፣ አሁንም ሰብአዊ ድጋፍን ይሻል፡፡ ተከታታዩ ድርቅ፣ በተፈጥሮ መዛባት የተከሠተ ነው፡፡ ስለዚህ በድርቁ ሳቢያ ከብቶቹን ያጣውን ወገን መልሰን ማቋቋም ይኖርብናል፡፡ ለዚኽም አንደኛ፥ በግብርና ጽሕፈት ቤት በኩል፥ የትራክተር፣ የዘር፣ እና የማዳበርያ ድጋፍ ስለተገኘ፣ ቅድሚያ ለተፈናቃዮቹ መሰጠት አለበት፡፡ ሌላው ደግሞ፣ በመንግሥት በኩል፣ በዚኽ በተረጂው ወገን ስም የተሰባሰበ ገንዘብ አለ፡፡ ከዚያ ገንዘብ፣ ለተፈናቃዮች የእንስሳት ግብይት አልያም በሌላ መልኩ ድጋፍ እንዲደረግ መንግሥትን ፈቃድ ጠይቀናል። እኛ የማገገሚያ መርሐ ግብር አሰናድተን ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል፣ ለገባሬ ሠናይ ድርጅቶች ሳይቀር አድርሰን ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን።

የቦረና ዞን፣ የሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊዎች አኀዝ ወደ 1ሚሊዮን47 ሺሕ ማሻቀቡን የገለጹት፣ የቦረና ዞን የአደጋ ስጋት አመራር ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ሊበን፣ ከእነኚኽ ውስጥ፣ ከ100 ሺሕ በላይ የሚኾኑቱ፣ በቋሚ ርዳታ ድጋፍ አለመካተታቸውን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት የተፈናቃዮች ጠቅላላ አኀዝ ከ300ሺሕ በላይ መድረሱን ጠቅሰው፣ ለዘለቄታው መልሶ ማቋቋሙ ሥራ፣ ሁሉም አካል የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

XS
SM
MD
LG