ካለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ፣ በቦረና ዞን መጣል የጀመረው ዝናም፣ ለነዋሪዎች ተስፋን ፈንጥቋል።ላለፉት ሦስት ዓመታት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ በጠናው ድርቅ፣ ክፉኛ ሲጎዱ የቆዩት አርብቶ አደሮች፣ አሁን ለመከር ክትቻ እየተዘጋጁ መኾኑን ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ በተለይ፣ ከአምስት ተከታታይ የዝናም ወቅቶች መታጎል በኋላ፣ የደከሙበት አዝመራ ለፍሬ መድረሱ፣ “የሰው እጅ ከመመልከት ያድነናል፤” ሲሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና፣ በአካባቢው ዝናም መጣሉን ተከትሎ፣ የከብቶች ዋጋ በከፍተኛ አኀዝ ማሻቀቡን ነዋሪዎቹ ሲገልጹ፤ የቦረና ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት በበኩሉ፣ የዞኑን ነዋሪዎች የኑሮ ዘይቤ ከአርብቶ አደርነት ለማላቀቅ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
አቶ ዲደ ሀሱማ፣ የቦረና ዞን፣ ያበሎ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። የእርሻ ሥራን ከጀመሩ ዐሥርት ዓመታትን ያስቆጠሩት አቶ ዲደ፣ በቦረና ዞን ለተከታታይ ወቅቶች የጠናው ድርቅ፣ ብዙ ከብቶችን እንደገደለባቸው፣ ለአምስት ተከታታይ አዝመራ የዘሩት ሰብልም፣ በዝናሙ መቅረት እንደጠፋባቸው ተናግረዋል። አሁን ግን የዘሩት ጤፍ ለመከር ክትቻ ሊደርስ እንደኾነ አመልክተዋል።
“ብዙ ጊዜ ዘር ዘርተን ጠፍቶብናል፡፡ ይህንም ቢኾን፣ ድርቁ እያየለ በነበረበት ጊዜ፣ የዝናሙ ወቅት በመድረሱ ብቻ ከእግዚአብሔር ጋራ ብለን ነው የዘራነው። ስንዘራ በነበረበት ወቅት፣ ሰዎች “ምን አይተኽ ነው የምትዘራው?” ሲሉኝ፣ ችግሩ ከላይ ሳይኾን ከእኛ ነው፤ ይልቁንስ ጸልዩልኝ፤ ብዬ ነው የዘራኹት። ከዘራኹት ከሁለት ቀናት በኋላ ዝናሙ ዘነመ፤ መሬቱም ረሰረሰ። ይህ ማሳ፣ ወደ 15 ሄክታር ይኾናል፤ ጤፍ፣ በቆሎ እና ሌሎችም ሰብሎች ተዘርተውበታል።”
በድርቁ ምክንያት ተራቁቶ የነበረው መሬት፣ የዝናሙን መጣል ተከትሎ በልምላሜ ተሸፍኗል፡፡ አቶ ኮሎላ ቆዶም፣ የያቤሎ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ድርቁ ብዙ ከብቶችን በመጨረሱ፣ መሬቱን አርሶ እና አለስልሶ ለአዝመራ ማብቃት አዳጋች እንደነበር ያወሳሉ፡፡
“ድርቁ ብዙ በመቆየቱ ለብዙ ችግር ዳርጎናል፡፡ እኛ አርሶ አደሮች ብንኾንም፣ ከብቶችንም እናረባለን፡፡ ዛሬ ከብቶቻችን አልቀዋል፤ ጥቂት ፍየሎች ብቻ ናቸው የቀሩን። ማሳውን ለዘር ለማዘጋጀትም በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ አንዳንዱ ሰዉን እንደ በሬ ጠምዶ ነው ያረሰው፡፡” ያሉት አቶ ኮሎላ “እንዲሁ ባዶ መሬትም ላይ ዘር የበተነ አለ፡፡ አሁን ዝናም ዘንሞልናል፤ ፈጣሪ ይመስገን፤ ከጉዳታችን የማገገም ተስፋን ፈንጥቆልናል።”
አክለውም” ዝናሙ አሁንም ቢቀጥል መልካም ነው፡፡ ለአጨዳ ሊደርሱ ያሉ ሰብሎች አሉ፤ ሌሎች ገና ዝናም የሚፈልጉ ተክሎችም አሉ፤ ኾኖም ዛሬ ላይ ደስተኞች ነን። ብለዋል።
አቶ ኮሎላ፣ በሰባት ሄክታር ማሳቸው ላይ፥ ስንዴ፣ ጤፍ እና ሌሎችንም ሰብሎች መዝራታቸውን ቢጠቅሱም፣ ዐሥር የቤተሰቦቻቸውን አባላት፣ ከመንግሥት በሚሰጥ ርዳታ እያኖሩ እንደኾነ ተናግረዋል። የዘሩት ሰብል ደርሶ፣ የሰው እጅ ከማየት እንደሚያላቅቃቸው ተስፋቸውን ገልጸዋል። አቶ ዲደ ሀሱማ፣ በዞኑ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች፣ ካለፈው የችግር ወቅት ተሞክሮ በመውሰድ፣ የኑሮ ዘይቤያቸውን ማጤን እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት፣ በቦረና የተከሠተው ድርቅ ክፉኛ ያጠቃው፣ የዞኑን የእንስሳት ሀብት ነው። የዞኑ አርብቶ አደር እና መስኖ ልማት ጽሕፈት ቤት፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጸው፣ ከዞኑ የከብት ሀብት ከ86 በመቶ ያላነሱት በድርቁ አልቀዋል። በወቅቱ፣ “ከብቶቻችን ይሞቱብናል፤” በሚል በአነስተኛ ዋጋ ይሸጡ የነበሩ ከብቶች፣ አሁን ዝናቡ መጣል ከጀመረ ወዲህ፣ ዋጋቸው በከፍተኛ አኀዝ መናሩ ታውቋል።
በያበሎ ወረዳ የሚገኝ ገበያ፣ ከቦረና ዞን የከብት ገበያዎች ትልቁ ነው። አቶ ቦሩ ገኛን ያገኘኋቸው በዚኽ ገበያ ውስጥ ነው። ከደርግ ሥርዐት ውድቀት ወዲህ፣ በብር ሁለት ሺሕ እና በብር አምስት መቶ የሚሸጥን ከብት ገና ዘንድሮ ነው ያየነው፤ ሰዉ በጣም ተቸግሮ ነበር፤ ለዘር እንኳን ይጠፋብናል፤ ብለን ሰግተን ሳለን ፈጣሪ ደረሰልን፡፡ አሁን ከኬንያ ሳይቀር ገብተው በ20 እና በ30ሺሕ ብር እየገዙን ነው።
በዚኹ ገበያ ነበር ያገኘናቸው አቶ ዶየ ዱለቻንም፤ “በአሁኑ ወቅት፣ ከብት ካለው ሰው ይልቅ የሌለው ይበዛል፡፡ የቤት እንስሳቱ ካለቁበት የሚበዛው ወደ ከተሞች ፈልሷል፡፡ ትላንት ከብቶቹን በሞት እንዳይነጠቅ፣ በትንሽ ዋጋ የገዛ ሰው፣ አሁን በጣም በናረ ዋጋ እየሸጠ ነው። እኔ ራሴ በድርቁ ጊዜ፣ ስምንት ወይፈኖችን በስምንት ሺሕ ብር ነበር የሸጥኹት፡፡ ያኔ ከእኔ በርካሽ የገዙት፣ አሁን በብር 10 እና 12 ሺሕ እየሸጡ ናቸው።” ብለዋል።
ዲደ ጃርሶ፣ የያበሎ ወረዳ ገቢዎች ቢሮ ባልደረባ ሲኾኑ፤ “ጊደሮች፥ እስከ ብር 16፣ 17 እና 18 ሺሕ እየተሸጡ ናቸው፡፡ ወይፈን ደግሞ ከብር 26 እስከ 28 ሺሕ ብር እየተገዛ ነው። ነጋዴዎች ካልኾኑ በቀር ነዋሪው በዚኽ የናረ ዋጋ ለመግዛት አይችልም፤ ምክንያቱም ያሉት ከብቶች በድርቁ አልቀውበታል፡፡ ድርጅቶች አልያም መንግሥት ካልደገፋቸው በስተቀር የመግዛት ዐቅም ይኖራቸዋል ብዬ አላስብም።” ይላሉ።
አቶ መሐመድ አባ ቆዳ፣ የቦረና ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሓላፊ፣ በዘንድሮ ክረምት፣ በዞኑ፣ ከ97 ሺሕ በላይ ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸዋል። የዘር፣ የማዳበርያ እና የእርሻ ድጋፍ አቅርቦቱ፣ ለሁሉም አርሶ አደሮች አለመዳረሱን ሓላፊው ጠቅሰው፣ የኦሮሚያ ክልል ለዞኑ አርሶ አደሮች፣ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ፣ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውቀዋል።
“ዝናም ካለ፣ በአርሶ አደር አካባቢ ሰብል መዝራት ይቻላል፡፡ እኛ ሁለት የዝናም ወቅቶች ነው ያሉን፡፡ የአካባቢው ነዋሪ፣ እንደምን ወደ እርሻ ሥራ ገብቶ ራሱን በምግብ ይችላል፤ በሚለው ላይ አቅደን እየሠራን ነው፤ አሁን ወደ ትግበራው ገብተናል።”
የዚኽን ሥራ ትግበራ፣ ከመሬት አስተዳደር ጋራ ኾነን እየሠራን ነው፤ ያሉት አቶ መሐመድ፣ በተለይ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ የአርብቶ አደሩን ሕይወት ወደ ቋሚ የኑሮ ዘይቤ ለመለወጥ ያወጣው ዐዲስ መርሐ ግብር፣ በትክክል በሥራ ላይ መዋል ሲጀምር፣ የዞኑ አጠቃላይ ነዋሪ ሕይወት ለመለወጥ እገዛ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡