የኬኔዲ የሰሜን ሸዋና የደቡብ ወሎ ዘገባዎች
ጋሸና ላይ በህወሓት ታጣቂዎች ሲቪሎች መገደላቸውን አስተዳደሩ ገለፀ

በጋሸና ከተማና በዙሪያዋ 280 የሚሆኑ ሲቪሎች በህወሓት ታጣቂዎች መገደላቸውን የጋሸና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ። ከተማዪቱ ውስጥ የሚገኙ 13 ተቋማት መውደማቸውንም የከተማው ከንቲባ አቶ ሞላ ፀጋው ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።
ህወሓት ግን መሰል ክሶችን ሲያስተባብል ይደመጣል።
ሪፖርተራችን ወደ አካባቢው ሄዶ የጋሸና ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
ዝርዝሩ ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ስለደረሰበት ጉዳት

የህወሓት ታጣቂዎች በወሎ ዩኒቨርሲቲ ላይ አደረሱ የተባለው ጉዳት 15 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ገልፀዋል።
ፕሬዚደንቱ በአካባቢው ጦርነት ባልነበረበት ወቅት ተዋጊዎቹ ዩኒቨርሲቲው ላይ ከባድ መሣሪያዎችን እንደተኮሱና በወቅቱ እርሳቸውም ቢሯቸው ውስጥ እንደነበሩ ተናግረዋል።
በመቀጠልም የዩኒቨርሲቲውን በርካታ ቁሳቁስና ንብረት ዘርፈው መወሰዳቸውንም የገለፁ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም ይህንኑ መስክረዋል።
ትግራይ ክልልን በማስተዳደር ላይ የሚገኙት ባለሥልጣናትና የህወሓት መሪዎች ለዚህ ክስ በቀጥታ ምላሽ ባይሰጡም ከዚህ ቀደም መሰል ክሦችን ሲያስተባብሉ መቆየታቸው ይታወቃል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያገኛሉ።
ሸዋሮቢት ውስጥ ተፈፅመዋል ስለተባሉ የመብቶች ጥሰቶች
የህወሓት ታጣቂዎች ሸዋሮቢት ውስጥ በቆዩባቸው ጥቂት ቀናት ፈፅመዋቸዋል ከተባሉ የመብቶች ረገጣ አድራጎቶች ውስጥ በወል እስከመድፈር የሚደርሱ ጥቃቶች ይገኛሉ።
ህወሓት እንዲህ ዓይነት አድራጎቶች በተዋጊዎቹ መፈፀማቸውን በተደጋጋሚ አስተባብሏል።
ሰሞኑን ወደ ሸዋሮቢት ተጉዞ የነበረው ኬኔዲ አባተ
“ሁከት ተፈፅሞናል፤ በሦስት እና በአራት የህወሓት ታጣቂዎች ተደፍረናል” ካሉ የከተማዪቱ ሴቶች ጋር ያደረገውን ውይይት ያካተተ ዘገባ ይዘናል።
ሃይቅ ውስጥ “በትንሹ 48 ሲቪሎች ተገድለዋል” - አስተዳደሩ
ሐይቅ ከተማ ውስጥ “በትንሹ 48 ሲቪሎች በህወሓት ታጣቂዎች ተገድለዋል” ሲል የከተማ አስተዳደሩ ክሥ አሰምቷል።
በከተማዪቱ ውስጥ የአዕምሮ ጤና ችግር የነበረባቸው ጭምር የጥቃት ዒላማ መሆናቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ሃሳባቸውን ያካፈሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ታጣቂዎቻቸው በሲቪሎችና ሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት እንደማይፈፅሙ የሚናገሩት የህወሓት መሪዎች በቅርቡ ባወጡት መግለጫ ጭምር ተመሳሳይ ክሦችን ያስተባብላሉ።
ሐይቅ ከተማና ጉዳቷ

ሐይቅ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭና የመንግሥት ተቋማት በሙሉ በህወሓት ጉዳት እንደደረሰባቸው የከተማ አስተዳደሩ ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት ለሰዉ አገልግሎት መስጠት የሚችል ተቋም እንደሌለ የከተማዪቱ ምክትል ከንቲባ መሱድ አበራ ገልጸዋል።
ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት አንዱ ከሆነው ሐይቅ ሆስፒታል “የህወሓት ታጣቂዎች መድኃኒቶችንና የህክምና መሣሪያዎችን ጨምሮ የሆስፒታሉን ንብረቶች ዘርፈው ሲወስዱ ማየታቸውን” አንድ የሆስፒታሉ ሃኪም ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችንና የተቋማት ውድመቶችን በተመለከተ የሚቀርቡባቸውን ክሦች፣ የህወሓት መሪዎች በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ።
የኮምበልቻ መጋዘን እንደገና ዝግጁ ነው

መንግሥት "ከ500 ሺህ ኲንታል በላይ የእርዳታ እህል በህወሓት ታጣቂዎች ተዘርፎበታል" ያለው የኮምበልቻ መጋዘን ለቀጣይ አገልግሎት መዘጋጀቱን ገለፀ።
ህወሓት ውንጀላውን አስተባብሏል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች በቂ ድጋፍ እየቀረበላቸው አለመሆኑን የገለፁ ሲሆን ዋነኛው ምክንያት የመጋዘኑ መዘረፍ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ተናግረዋል።
መንግሥት በቀጣይነት በጦርነቱ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ከፍተኛ መጠን ያለው እህል ከውጭ በማስገባት ላይ እንደሆነ፣ የኮምበልቻው መጋዘንም ለአገልግሎት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ።
የደሴ ሆስፒታል ማከም ጀመረ

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቀለል ያሉ የህክምና አገልግሎቶችን መስጠት መጀመሩ ተገለፀ።
የሰማንያ ዓመታት ዕድሜ ያለው ይህ ሆስፒታል “የህወሓት ታጣቂዎች ውድመትና ዘረፋ አድርሰውበታል” ከተባለ በኋላ አሁን የህክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው የራሱ መሣሪያዎች እንደሌሉት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ኃይማኖት አየለ ለቪኦኤ ተናግረዋል።
ቀለል ያሉ አገልግሎቶችን መስጠት የተጀመረው በሃኪሞቹ ልምድና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመተጋገዝ መሆኑንም ሥራ አስኪያጇ አመልክተዋል።
“ታጣቂዎቹ ሲቪሎችንና ሲቪል ተቋማትን ዒላማ አድርገዋል” በሚል የሚቀርቡባቸውን ክሶችን የህወሓት መሪዎች ሲያስተባብሉ ቢቆዩም የአማፂው ኃይሎች በአማራ ክልል በቆዩናቸው አካባቢዎች አርባ ሆስፒታሎችንና 453 የጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ በርካታ የጤና ተቋማትን ማውደማቸውንና ዘረፋ መፈፀማቸውን” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ገልፀዋል።
ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የጦርነት ወላፈን በሐይቅ

የህወሓት ኃይሎች የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተቆጣጥረው በነበሩባቸው ወራት ሰላማዊ ሰዎችን እና የመኖሪያ አካባቢዎችን ዒላማ አድርገዋል ሲሉ ነዋሪዎችና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎዪቱ ሐይቅ ከተማ በአንድ መኖሪያ ቤት አባትና ልጅን ጨምሮ አራት ሰዎች በውጊያ ወቅት በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ሦስቱ በአንድ ቀን የተገደሉ ሲሆን አስከሬኖቻቸውም ግቢው ውስጥ በአንድ መቃብር እንዲያርፉ መደረጉን፣ አራተኛዋ ደግሞ ህይወቷ ያለፈው በቀጣዩ ቀን በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ መሆኑና ጦርነቱ ከተማዪቱ ውስጥ ለቀናት መካሄዱን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ በኮምቦልቻ

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀውና ራሳቸውን የትግራይ ሠራዊት ብለው የሚጠሩት የህወሓት ታጣቂዎች ኮምቦልቻ ከተማን ተቆጣጥረው በነበሩትበት ከጥቅምት 21 እስከ ኅዳር 27/2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መጋዘኖች ተሰብረው ከ100 ሺሕ ኩንታል በላይ የእርዳታ አህል መዘረፉን ኮሚሽኑ አስታወቀ።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መጥፎ አሻራ ካሳረፈባቸው ከተሞች አንዱ ወደ ሆነው ደሴ ከተማ ተጉዞ ሰሞኑን ቆይታውን ሲያካፍለን የነበረው ዘጋቢያችን ኬኔዲ አባተ ዛሬ ደግሞ ኮምቦልቻ ከተማ ይገኛል።
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።