በሶማሊያ የመኪና አደጋ 11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞቱ

Your browser doesn’t support HTML5

ሶማሊያ የመኪና አደጋ 11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞቱ

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም)፣ በሶማሊያ ቦሳሶ አካባቢ በደረሰ የመኪና አደጋ፣ 11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሞታቸውን አስታወቀ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በአጋጠመው በዚኹ አደጋ፣ ቢያንስ 20 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተቋሙ መግለጫ አክሎ አመልክቷል፡፡ ስደተኞቹ፥ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በመጓጓዝ ላይ እንደነበሩ የጠቀሰ ሲኾን፣ የዔደን ባሕረ ሠላጤን በማቋረጥ ወደ የመን ለመሻገር ዕቅድ እንደነበራቸው አይ.ኦ.ኤም ገልጿል፡፡

የተቋሙ የምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ቃለ አቀባይ ይቮኒ ንደጌ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ የአደጋውን ሰለባዎች ዝርዝር መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ ሟቾቹ ስደተኞች፥ ኢትዮጵያውያን እንደኾኑ እናምናለን፤ ብለዋል፡፡ ባለፉት ዓመታትም፣ በዚኹ የሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች መስመር፣ በርካቶች እንደ ሞቱ፣ የደረሱበት እንደጠፋ እና በባሕር እንደሰጠሙም ቃለ አቀባዩ አውስተዋል፡፡

ስደተኞቹ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት፣ በሶማሊያ ቦሳሶ በኩል አድርገው፣ የዔደን ባሕረ ሠላጤን በማቋረጥ ወደ የመን ለመሻገር ዐቅደው እንደነበርም አይኦኤም በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

አደጋው በደረሰበት ስፍራ የነበሩ የአካባቢው ሰዎች፣ የ11 ተሳፋሪዎችን አስከሬንና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን 20 ሰዎች፣ ወደ ቦሳሶ አጠቃላይ ሆስፒታል መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡ ኾኖም ተቋሙ፣ የተጎጂዎቹን ዝርዝር መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ፣ የአይኦኤም የምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ቃለ አቀባይ ይቮኒ ንደጌ ተናግረዋል፡፡

“የስደት መስመሮቹ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚለዩ ናቸው፡፡ ከአካባቢው ባለሥልጣናት እና ከጸጥታ አካላት እይታ ለመሰወር ተብሎ ስለሚዘጋጁ፣ እንዲህ ዐይነት አደጋ በሚደርስበት ጊዜ እንኳን መረጃ ለማግኘት አዳጋች ይኾናል፡፡” ካሉ በኋላ “የስደት መስመሮቹ በጣም ሩቅ ናቸው፤ ጉዞውም በጨለማ ነው የሚደረገው፡፡ ስለዚህ በዚኽ አደጋ ያለቁት ስደተኞች ዝርዝር መረጃ፣ በትክክል ምን እንደኾነ አናውቅም፤ ማንነታቸውን በተመለከተ ግን፣ የኢትዮጵያ ዜጎች እንደኾኑ ነው የምናምነው፡፡” ብለዋል።

የስደት መስመሮቹ፣ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚለዩ ናቸው፡፡ ከአካባቢው ባለሥልጣናት እና ከጸጥታ አካላት እይታ ለመሰወር ተብሎ ስለሚዘጋጁ፣ እንዲህ ዐይነት አደጋ በሚደርስበት ጊዜ እንኳን መረጃ ለማግኘት አዳጋች ይኾናል፡፡”

አይኦኤም፣ የአሁኑን አደጋ ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ወደ የመንና ሳዑዲ አረቢያ በሚደረግ ሕገ ወጥ ስደት ምክንያት፣ ወደ 1ሺሕ100 ስደተኞች መሞታቸውንና መጥፋታቸውን አሳውቋል፡፡ የአይኦኤም የምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ቃለ አቀባይዋ ይቮኒ ንደጌም፣ የምሥራቁ የስደት መስመር አሳዛኝ ክሥተቶችን በተደጋጋሚ እንደሚያስተናግድ ገልጸዋል፡፡

“ኣይኦኤም፣ ይህን የመሰሉ አሳዛኝ አደጋዎችን መዝግቧል፡፡ ባለፉት ዓመታት፣ ከምሥራቅ አፍሪካ፣ በዋናነትም ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ እና ከኢትዮጵያ፣ ከዚኽ የስደት መስመር በመነሣት፣ በዔደን ባሕረ ሠላጤ አድርገው ወደ የመን ለመሻገር የሞከሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡” ያሉ ሲኾን “ስደተኞቹ ይህን የሚያደርጉት፣ ወደ የመን ድንበር ለመድረስ እና ከዚያም የሥራ ዕድል ፍለጋ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ወደ ሌሎችም የሠላጤው ሀገራት ለመሸጋገር ነው፡፡ በዚኽ መሰሉ አሳዛኝ የመንገድ ላይ አደጋ ምክንያት ከሚያልቁት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በተጨማሪ፣ በርካቶች የዔደን ባሕረ ሠላጤን ሲያቋርጡ ባሕር ውስጥ ሰጥመው እንደሚሞቱ እናውቃለን፡፡ በዚኹ መስመር፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችም ጠፍተው እንደ ቀሩ ይታመናል።” ብለዋል።

የስደተኞች ተቋሙ መግለጫ እንደሚያሳየው፣ ከሦስት ዓመታት በፊት፣ በኢትዮጵያ የተደረገ አንድ የቤተሰብ ጥናት፣ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ ብቻ፣

50ሺሕ የሚኾኑ ሰዎች እንደ ወጡ መቅረታቸውን ቤተሰቦች አመልክተዋል፡፡ የጸጥታ ችግር እና የገንዘብ እጥረት፣ የተሟላ ጥናት ለማድረግ ዕንቅፋት ስለሚኾኑ እንጂ፣ ቁጥሩ ከዚኽም በላይ ሊኾን እንደሚችል መግለጫው ያሳያል፡፡

ስደተኞች፣ በሶማሊያ እና በጅቡቲ በኩል አድርገው፣ ወደ የመንና ሳዑዲ አረቢያ የሚሔዱበት የምሥራቁ መስመር፣ ዋናው የሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች መተላለፊያ እንደኾነ መግለጫው አሳይቷል፡፡ በመስመሩ የሚሰደዱት አብዛኞቹ ሰዎችም፣ ድህነትን፣ ድርቅንና ግጭትን ሸሽተው ከሀገራቸው የሚወጡ ኢትዮጵያውያንና ሶማልያውያን እንደኾኑ ተገልጿል፡፡

ስደተኞቹ በጉዟቸው ወቅት፥ ለግርፋት፣ ለእገታ፣ ለእስር፣ ለአስገድዶ መድፈር፣ ለዘመናዊ ባርነት እና ለአካላዊ ጥቃት እንደሚዳረጉ መግለጫው አትቷል፡፡ ይህም ኹሉ ኾኖ፣ በዚኹ መስመር የሚጓዙት ሰዎች ቁጥር፣ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ እንደኾነ መግለጫው አመልክቷል፡፡ በዚህ ዓመት በጥር እና በየካቲት ወራት ብቻ፣ አይኦኤም 21ሺሕ469 ስደተኞች፣ በዚኹ መስመር ወደ የመን መግባታቸውን መዝግቤአለኹ፤ ይላል፡፡ ይህ አኀዝ፣ ካለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ከተመዘገበው 14ሺሕ298 ስደተኞች ጋራ ሲነጻጸር፣ ብላጭ እንደሚያሳይ መግለጫው አትቷል፡፡