በሁለት ትናንሽ ጀልባዎች ባህር አቋርጠው ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ ሊገቡ ከነበሩ ፍልሰተኞች መካከል ትናንት ረቡዕ አራቱ መሞታቸው ተነገረ፡፡ ከዚህ በፊትም በደረሰ ተመሳሳይ አደጋ ሰዎች ቢሞቱም ከፈረንሳይ እየተነሱ ወደ እንግሊዝ የሚጓዙ ፍልሰተኞች አሁንም የባህር ላይ ጉዟቸውን መቀጠላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በፈረንሳይ የባህር ዳርቻ የምትኖር ፋቢዮላ ሪከባስ የተባለች የአካባቢ ነዋሪ ትናንት ረቡዕ ታህሳስ 5/ 2015 በፍልስተኞች የተሞሉ ጀልባዎች አካባቢውን ለቀው ሲወጡ አይታለች፡፡
ሪከባስ ህጻናት ጭምር የተሳፈሩባቸው ትናንሾቹ ጀልባዎች ከጧቱ 2 ሰዓት ኣካባቢው ለቀው ሲወጡ ብታይም በሰላም ስለመድረሳቸው ግን እርግጠኛ አይደለችም፡፡
“ዛሬ ጠዋት ከባህሩ ጥቃቅኖቹን የሽሪምፕ ዐሳዎች ለማጥመድ ወደ ባህሩ ስሄድ በሚሳዛያዝን ሁኔታ ህጻናት ጭምር ያሉበት ፍልሰተኞች የተሞሉ ሁለት ጀልባዎችን አይቼ ነበር፡፡ በእውነቱ በጣም እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡ በሰላም ይደርሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ከሁሉም በላይ አንጀቴን በጣም የበላኝ የጨቅላዎቹ ህጻናት ነገር ነው፡፡ በጣም የሚያሰቅቅ በየቀኑ የሚደረግ ነገር ነው፡፡ በእውነት እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡”
ትናንት ረቡዕ ጧት በረዶ በሆነው የእንግሊዙ የባህር መተላለፊያ ከፈረንሳይ የባህር ዳርቻ የተነሱ ፍልሰተኞችን ጭና ስትጓዝ የነበረች ጀልባ የመስጠሟ ዜና ከተነገረ በኋላ ነበር ሪካባስ ይህን የተናገረቸው፡፡
በአደጋው አራት ሰዎች መሞታቸውን የብሪታኒያ መንግሥት አስታውቋል፡፡
የነፍስ አድን ጀልባዎች ሂሊኮፐተሮች እና ህይወት አድን ቡድኖች ከፈረንሳይና ብሪታኒያ የባህር ሃይል ጋር በመሆን ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት እየሰሩ መሆኑ ተነግሯል፡፡
አደጋው የደረሰው ፍልሰተኞችን ወደ እንግሊዝ አስርገው ለማስገባት ሰዎችን በህግ ወጥ የሚያዘዋውሩ የተደራጁ የውንብድና ቡድኖችን ጉዳይ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሽ ሱናክ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት በሰጠበት ጊዜ መሆኑን ተመልክቷል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የመንግሥት ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡
ይኸኛው አደጋ የደረሰው ህዳር 2014 ዓም ከባህሩ ላይ መንሳፈፍ በተሳናት ትንሽ ጀልባ ወደ እንግሊዝ ለመግባት ሲጓዙ ህይወታቹን ያጡ 27 ሰዎች ትልቁ አደጋ ሆኖ ከተመዘገበበት አንድ ዓመት በኋላ ነው፡፡
በመላው ብሪታኒያ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ቅዝቅዜው እጅግ የበረታ ሲሆን በከፊል የአገሪቱ ክፍል በረዶ ጥሏል፡፡
ቅዛዜው እጅግ የከበደ ቢሆንም ከላፈው ቅዳሜና እሁድ ወዲህ ብቻ እንኳ ከ500 በላይ የሚሆኑ ፍልሰተኞች አደገኛ ጉዟቸውን በእነዚያ ትናንሽ ጀልባዎች አድርገዋል፡፡
በጥቃቆኖቹ ጀልባዎች ጉዙውን የሚያቀናጁት ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በቅዝቃዜው የደከመውን የባህር ላይ ነፋስና የተረጋጋውን ባህር አጋጣሚ በመጠቀም ብዙ እያተረፉ መሆኑ ተመልክቷል፡፡