በሱዳኑ አራተኛ ቀን ውጊያ የሟቾች ቁጥር ወደ 200 ተቃረበ

  • ቪኦኤ ዜና

ፀጥታ የሰፈነበት የካርቱም ጎዳና እአአ 18/2023

በሱዳን፣ በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ውጊያ፣ አራተኛ ቀኑን በአስቆጠረበት በዛሬው ዕለት፣ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ወደ 200 መቃረቡ ሲዘገብ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን፣ ሁለቱም ወገኖች ውጊያውን ለማቆም እንዲስማሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ የተቀሰቀሰው ውጊያ፣ አራተኛ ቀኑን በያዘበት በዛሬው ዕለት፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን፣ የተፋላሚ ኃይሎች መሪዎችን በስልክ በማነጋገር፣ ሁለቱም ወገኖች ውጊያውን ለማቆም እንዲስማሙ ጥሪ አቅርበውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተፋላሚ መሪዎቹን ያነጋገሯቸው፣ ትላንት ሰኞ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማሲያዊ አጀብ ተሽከርካሪዎች ላይ ተኩስ መከፈቱን ተከትሎ መኾኑን አመልክተዋል። በጥቃቱ፣ በአንድም ሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱ የተገለጸ ሲኾን፣ በአስቸኳይ ተኩስ መቆም እንዳለበት እንደሚያሳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

“ዛሬ ጠዋት፣ የሱዳን የጦር ኃይሎች አዛዥ ጀነራል አብዱል ፈታሕ አብደል ራህማን አል ቡርሃንንና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሎቹን መሪ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን አነጋግሬያለኹ፤” ያሉት አንተኒ ብሊንክን፣ በዲፕሎማቶቻቸው ላይ የሚሰነዘር ምንም ዐይነት ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው በግልጽ እንዳሳሰቧቸው አስታውቀዋል፡፡

ትላንት የደረሰውን ድንገተኛ ጥቃት በሚመለከት፣ ምርመራ በመካሔድ ላይ እንዳለ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ድርጊቱ የተፈጸመው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ በኾኑ ወገኖች ስለመኾኑ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙ ገልጸዋል።

ሁለቱም ወገኖች ውጊያውን እንዲያቆሙ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚቀርበው ተማጽኖም እንደቀጠለ ነው።