በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ዛሬም ተቃውሞ ቀጥሏል


ከአምቦ ከተማ ባለፈው ሃምሌ ወር ታስሮ በአዲስ አበባ እስር ቤት ሳለ ታሞ ሆስፒታል ህይወቱ እንዳለፈ የተገለጸው ተማሪ አብደታ ኦላንሳ ቀብር ዛሬ በአምቦ ከተማ ተፈጽሟል። የጸጥታ ሃይሎች ቀብር ሥነ ስርዓቱን ለማስተጓጎል ድብደባና እስር ፈጽመዋል። ትናንት አስከሬኑን ለመቀበል ተኩሰው የገደሉትም አለ ብለዋል።

ባለፈው ሐምሌ ወር ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ ታስሮ እንደነበርና ታሞ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና ላይ ሳለ ህይወቱ እንዳለፈ የተነገረው ተማሪ አብደታ ኦላንሳ ቀብር ዛሬ አምቦ ከተማ ተፈጽሟል። በስልክ ያነጋግርናቸው ነዋሪ ትናንት ማታ የወጣቱን አስከሬን ለመቀበል በወጣ ህዝብ ላይ የጸጥታ ሃይሎች ድብደባ አድርሰዋል። ወደ ሰማይ ሲተኩሱም ነበር። አንድ ሰው በጥይት ተመትቶ ተገድሏል ብለዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአምቦው ነዋሪ አስከትለውም ዛሬ በቀብሩ ላይም እንዲሁ የከተማው ነዋሪ በብዛት ወጥቶ እንዳይቀብረው ለማስተጓጎል ወታደሮች በተለይ ወጣቶችን መኪና ላይ እየጫኑ ወስደዋቸዋል ብለዋል። ወደ ቀብሩ ጉዞ ላይ የነበረ ወጣት በጥይት መገደሉን ገልጸውልናል።

ትናንትና ደግሞ በአምቦ ዩኒቨርስቲ አዋሮ ግቢ አጠገብ የአንድ ወጣት አስከሬን ተገኝቷል ብለዋል።

የአምቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ሂርኮ አምቦ ውስጥ ተገደሉ የተባለውን አስተባብለዋል።

ባልደረባችን ጃለኔ ገመዳ አነጋግራቸው ነበር ። “ባለው መረጃ አምቦ ውስጥ የተገደለ ሰው የለም አዲስ አበባ ከተማ ታሞ የሞተ ሰው አአስከሬኑ አምቦ ገብቶ ዛሬ ተቀብሯል ። ለበለጠ መረጃ የአምቦ ከተማ ከንቲባውን አነጋግሩ” ሲሉ ቢመሯትም ከንቲባ ዱጋሳ ኦሉማ በእጅ ስልካቸው በተደጋጋሚ ተደውሎ አላነሱትም።

አዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሞቶ ዛሬ ተቀበረ ስለተባለው ወጣት አብደታ ኦላንሳ ጉዳይ ሆስፒታሉ መዝገቡን ተመልክቶ ነገ ማብራሪያ ሊሰጥ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ሶራ ሃለኬ ባገኘው መረጃ ደግሞ ፌደራል ፖሊሶች የተማሪዎች መኝታ ቤቶች እየገቡ ጭካኔ የተመላበት ድብደባ አካሂደዋል ብዙ መቶዎች አስረው ወስደዋል።

ስሜን አትግለጡ ያለው ተማሪ፣ ተማሪዎች ያሉትን ለማጣራት ወደ ከተማዋ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ደውሎ እንዳልተሳካለት ባልደረባችን ሶራ ሃላኬ በዘገባው አመልክቷል።

በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ ደግሞ የከተማው መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች “የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት የታሰሩ ተማሪዎች ይፈቱ” “ ግድያው ይቁም “ በማለት ትናንትናና ዛሬ ሰልፍ ወጥተዋል ሲሉ “ ስማችንን እንዳትገልጹብን” ያሉ ተማሪዎች ለባልደረባችን ቱጁቤ ሆራ ገልጸውላታል።

በሰላም ነበር ሰልፉ የሚካሄደው የመንግሥት ሃይሎች በተኑት፣ የተወሰኑ ተማሪዎች ተደበደቡ፣ የታሰሩም አሉ ያለው ተማሪ እኔም ራሴ ከተደበደቡት አንዱ ነኝ ብሏል።

“የሃሮማያ እና የጅማ ተማሪዎች እንዲሁም በአምቦ ተማሪዎች መገደላቸውን በመቃወም፣ ድርጊቱ ይቁም ትግላችን ይቀጥላል ብለን ድምጻችንን ስናሰማ ነበር” ሲል ገልጿል።

የሻሸመኔ ከተማ የአስተዳደር እና ደህንነት ሐላፊ አቶ ስንታየሁ ጥላሁን ግን ሃሰት ነው ይላሉ ።

“ሰልፍ የወጣ የለም። ሰልፍ ማካሄድ ተፈቅዷል፣ ግን የወጣም የለም የታሰረም የለም፣ ተማሪዎች እየተማሩ ናቸው። መማር የፈለገ ይማራል፣ የማይፈልገውን ግን አናስገድድም መብቱ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ስንታየሁ አንዳንድ ጥያቄ ያነሳ ሊኖር ይችላል ብለው ነበርና ቱጁቤ ምን ጥያቄ ነው ያነሱት? ብትል “ማለት የጠየቁት እኮ ነገር የለም ቢሯችን የደረሰው መረጃ የለም ከተማውም ሰላም ነው” እንዳሏት አክላ ጠቅሳለች።

XS
SM
MD
LG