ከ1992 ዓ.ም እስከ 2000 ድረስ ባለው ጊዜ በተለያየ መንገድ ኖርዌይ ገብተው የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው የነበሩ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ሶማሌያውያን ናቸው፤ በኖርዌይ ያገኙትን ዜግነት የተነጠቁትና የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው የነበሩትም እንዳይታደስላቸው እግድ የተጣለባቸው።
የኖርዌይ መንግሥት የአብዛኞቹን የፌስቡክ ገጾች ሲመረምር ግለሰቦቹ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን አቅርበው በነበረበት ወቅት የሰጡት መረጃ እና ስለ እራሳቸው አሁን የሚለጥፉት መረጃ የተለያያ ኾኖ እንዳገኘውና ይህንንም መሠረት አድርጎ ተጨማሪ ማጣራት ሲያደርግ ዋሽተዋል ብሎ በማመኑ ዜግነታቸውን እንደነጠቃቸው አስታውቋል።አቶ በሻሕ ሙሴ
በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ ምክር ቤት ተመራጭ የኾኑት አቶ በሻህ ሙሴ መሐመድ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፤ ግለሰቦቹ ለኖርዌይ መንግሥት ያቀረቡት የጥገኝነት ጥያቄ፤ ሶማሌያ ውስጥ በተፈጠረው አለመረጋጋት መኖር ባለመቻላቸው መሰደዳቸውን በማስረዳት ነው። ይህ ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝቶ አንዳንዶቹ ዜግነታቸውን ካገኙ 16 ዓመታት አስቆጥረዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው ኑሮአቸውን ቀጥለዋል።
የኖርዌይ የፍልሰተኛ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት፤ እነዚህ ዜጎች የዜግነቱንም ኾነ የመኖሪያ ፈቃዱን ያገኙት በሐሰት ላይ በተመሰረተ መረጃ እና ማስረጃ ነው የሚል ጥቆማ ስለደረሰው ለሁለት ዓመት ምርመራ አድርጌያለሁ ማለቱን አቶ በሻሕ ሙሴ ይናገራሉ።
“የኖርዌይ መንግሥት መረጃዎቹን አሰባሰብኩ ካለበት መንገዶች አንዱ የሰዎቹን የፌስቡክ ገፆች ነው። መንግሥቱ የአብዛኞቹን የፌስቡክ ገጾች ሲመረምር ግለሰቦቹ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን አቅርበው በነበረበት ወቅት የሰጡት መረጃ እና ስለ እራሳቸው አሁን የሚለጥፉት መረጃ የተለያያ ኾኖ እንዳገኘውና ይህንንም መሠረት አድርጎ ተጨማሪ ማጣራት ሲያደርግ ዋሽተዋል ብሎ በማመኑ ዜግነታቸውን እንደነጠቃቸው አስታውቋል”
አቶ በሻሕ አያይዘው፤ የኖርዌይ የፍልሰተኛ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት አገኘሁት ባለው የምርመራ ውጤት፤ አንዳንዶቹ ሶማሌያውያን ነን ከሞቃዲሾ ነው የመጣነው ብለው ጥገኝነት ጠይቀው ፌስቡካቸው ላይ የጅቡቲ እና የሌሎች ጎረቤት ሀገር ዜጎች መኾናቸውን የሚያሳይ ፎቶ ግራፍና ቪዲዮ ለጥፈዋል።
ከጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸ ጋር የተነሷቸ ፎቶዎች፣ የሚለዋወጧቸው መልዕክቶች ፈጽሞ ካቀረቡት ታሪክ ጋር እንደማይሄድ ተነግሯል። አንዳንዶቹ ደግሞ መኖር አልቻልንም ወዳሉት ሀገር ተመልሰው መሄዳቸውን መኖሪታ ቤትና ንግድቤት
መስራታቸውን የሚያሳዩ ምስሎች እና አስተያየቶች ማስፈራቸው የኖርዌይ የፍልሰተኞች ጉዳዮች መሥሪያ ቤቱ ደርሼበታለሁ ይላል።
መሥሪያ ቤቱ ይህንኑ በፌስ ቡክ ላይ የሰፈረ መረጃ ተከትሎም ምርመራ ሲያደርግ አንዳንዶቹ በጭራሽ ሶማሌኛ ቋንቋ የማይችሉና ሶማሌያ ከምትባለው አገር ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የጎረቤት ሀገር ዜጎች ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌላ ሶማሌኛ ቋንቋ ተናጋሪ ከኾኑ ጎረቤት አገራት የመጡ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ያደረጓቸው የመልዕክት ልውውጦች እና ወደ ቤተሰቦቻቸው የላኩት ገንዘብ በማስረጃ ተያይዞባቸዋል ተብሏል።
አሁን አሁን አገራት እንደ ፌስቡክ ባሉ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚውጡ ታሪኮችን እንደ የጀረባ ታሪክ ማጣሪያ መንገድ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የዩናይትድ ስቴትስ የሠራተኛ አስተዳደር ጉዳዮች ቢሮ የተቀጣሪ ሠራተኞቹን የደህንነት ዳራ ፍተሻ ለማጥራት አዲስ ለሕዝብ ክፍት የኾኑ ማኅበራዊ ድረ ገፆች ላይ የጀመረውን ዘዴ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።
አቶ በሻህ ሙሴም የኖርዌይ የፍልሰተኞች ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ሌላ እያጣራቸው የሚገኙ ሰዎች እንዳሉ ተናግሯል። በዚህ ምክንያት ብቻ የኖርዌይ ዜግነታቸው መነጠቃቸው፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው እንዳይታደስ መከልከሉ እና ወደየ አገራቸው ይመለሳሉ መባሉን በመቃወም ፊርማ አሰባስበው አቤቱታቸውን ሊያቀርቡ ነው ብለዋል።
የቬኦኤ ሶማለኛ ቋንቋ ዘገባን ጽዮን ግርማ አጠናቅራዋለች። ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።