በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሃይማኖትና ዲፕሎማሲ


በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ውስጥ ሃይማኖት ሁልጊዜ ቁልፍ ቦታ እንደነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ፤ ሁልጊዜ ተገቢው ግንዛቤ እንደማይሰጠው ተናግረዋል።

“ሃይማኖትና ዲፕሎማሲ - አንዱ አንዱን ሲያቋርጥ፤ ወይም መስቀለኛ ሲሆኑ” - በቴክሳስ ጠቅላይ ግዛቱ ራይስ ዩኒቨርሲቲ ተዘጋጅቶ ትናንት ንግግሮች የተደረጉበት ጉዳይ ነው።

በውይይቱ ላይ ሃሣባቸውን ያሰሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪ የዓለም የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ካርታ ሲሠመርና ድንበሮች ሲደነገጉ ሃይማኖት ዋና የሚባል ድርሻ ነበረው - በመላ የታሪክ ዑደት ውስጥ - ብለዋል።

ጃን ኬሪ በ2005 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን እንደተረከቡ በመሥሪያ ቤታቸው ውስጥ የሃይማኖትና የዓለምአቀፍ ጉዳዮች ቢሮ ፈጥረዋል።

ቢሮው የተከፈተው የፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደር በበርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረጉ ትብብሮችን ለማጠናከር የወሰደውን ተነሣሽነት ተግባራዊ ለማድረግ ነበር።

ቢሮው ባለፈው ዓመት ናይጀሪያ ውስጥ የሃይማኖት መሪዎች በሙስና ላይ የተነጋገሩበትን አውደጥናት በጋራ ማዘጋጀትና ማካሄዱን ኬሪ አስታውሰዋል።

በዚያ አውደጥናት ላይ የናይጀሪያ የሃይማኖት መሪዎቹ በየደረጃው የለውጥ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያግዝ የተግባር መርኃግብር ማውጣታቸውን ኬሪ ጠቁመዋል።

ኬሪ በቴክሳሱ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ “ሰዎች የመረጡትን እምነት የመያዝ፣ የመለወጥ፣ በእምነታቸው የማምለክ፣ ያለአንዳች ፍርሃትና መሸማቀቅ ስለእምነታቸው የመናገርና የማስተማርም ነፃነት ሊኖራቸው እንደሚበ እናስባለን” ብለዋል።

“ይህ የእምነትና የጎሣ ማንነት ነፃነት ደግሞ - አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኬሪ - በቁጥር ምክንያት የሚሰፋና የሚጠብብ አይደለም፤ ሕዳጣን፣ ከብዙኃኑ ጋር እኩል የእምነት ነፃነት ነው ሊኖራቸው የሚገባ።”

እሥላማዊ መንግሥትን የመሳሰሉ ፅንፈኛ የሁከት ቡድኖች በእምነት ሸማ ሥር እየተጠለሉ እጅግ የከፉ የጭካኔ አድራጎቶችን እንደሚፈፅሙ፣ ይህ ጭካኔአቸው ደግሞ ሕዳጣን በሆኑ እምነቶች ተከታዮች ላይም መድረሱን ኬሪ አስታውሰዋል።

ሃይማኖትና ዲፕሎማሲ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:12 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG