የዩናይትድ ስቴይትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ እራሱን የእስልምና መንግስት ብሎ በሚጠራው ቡድን (ዳይሽ) የሚፈጸሙ ግድያዎች በጂምላ ዘር ማጥፋትን ያካትታሉ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ።
“የደረስኩበት ውሳኔ ዳይሽ በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች በተለይ በክርስቲያኖች፣ ያዚዲስ እና ሽያ ሙስሊሞች ላይ የጂምላ ዘር ማጥፋት ይፈጽማል የሚል ነው።” ይላሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ። “ዳይሽ እራሱን የዘር አጥፊ ቡድን አድርጎ በርእዮተ ዓለምም ሆነ በተግባር አረጋግጧል። ይሄንን ደግሞ ከሚናገሩት፣ ከሚያምኑትና ከሚሰሩት በግልጽ መመልከት ይቻላል።” ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ አክለውም አሸባሪ ቡድኑ በሰው ዘር ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎችና የተለዩ ህዝቦችን ሕልውና በመፈታተን ማጥፋት ወንጀሎችም እጁ አለበት ብለዋል።
ሚስተር ኬሪ እነዚህን ድምዳሜዎች ያጠናከረላቸው በዩናይትድ ስቴይትስ ከፍተኛ የደህንነትና ስለላ መረጃዎች የቀረቡ ዘገባዎች እንደሆኑም ገልጸዋል። በነዚህ ዘገባዎች መሰረት እራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው ቡድን የተለየ ሃይማኖት ያላቸውን በእምነት ልዩነት የተነሳ ያለፍርድ ይረሽናል፣ በቡድን ይገድላል አስገድዶ ይደፍራል።
የዩናይትድ ስቴይትስ ኮንግረስ የባራክ ኦባማ አስተዳድር በኢራቅና ሶሪያ በእስላማዊ መንግስት የሚፈጸሙ ሀይማኖትና ብሄርን ያማከሉ ግድያዎችን በይፋ አጣርቶ የጭካኔ ድርጊቶቹን እንዲያወግዝ ለዛሬ የጊዜ ገደብ ሰጥቶ ነበር። የኬሪ ድምዳሜም የጊዜ ወሰኑን የጠበቀ ሆኗል።
የኔብራስካው ህዝብ ተወካዩ ጄፍ ፎርትንበሪ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ሰዎችን በቡድን እየለዩ መግደል ሲጀመር፤ ጉዳዩ የፍትህ ማጣት ብቻ ሳይሆን፤ በስብእናችንና ስልጣኔያችን ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴይትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደዚህ አይነት መግለጫ ለመጨረሻ ጊዜ ያወጣው ከ12 ዓመታት በፊት ሲሆን፤ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሊን ፓወል በሱዳን ዳርፉር ግዛት የተፈጸሙ ግድያዎችና የጅምላ አስገድዶ መድፈር ተግባሮችን “ዘር ማጥፋት” ብለውት ነበር።