ታላቁ የኅዳሴ ግድብ Great Reninssance
በኅዳሴ ላይ ድርድሩ እየተካሄደ ነው
ከሳምንታት በፊት በኅዳሴው ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው የግብፅ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ ውይይት ሲቋረጥ ሱዳን ተጨማሪ ጊዜ ከጠየቀች በኋላ የሦስቱ ሃገሮች የቴክኒክ ባለሞያዎች እንደገና ለድርድር መቀመጣቸው ተነገረ።
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የባለሞያዎቹ ቡድኖች በነዚህ መነጋገሪያ ዋና ዋና ነጥቦች ምን እንደሚሆኑን አስረድተዋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
See all News Updates of the Day
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች ኀይል ማመንጨት ጀመሩ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች፣ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ኀይል ማመንጨት መጀመራቸውን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል፡፡
እያንዳንዱ ተርባይን 400 ሜጋ ዋት ኀይል እንደሚያመነጭ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ ሦስት ተጨማሪ ተርባይኖች ሥራ እንደሚጀምሩም ጠቁመዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ወደ መጠናቀቅ እያመራ ስለመኾኑ እየተገለጸ ያለው፣ ከታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት የሚነሡ ስጋቶች እና ተቃውሞዎች በቀጠሉበት ወቅት ነው፡፡
ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነትን ማጽደቋን ኢትዮጵያ አደነቀች
ደቡብ ሱዳን፣ የናይል ተፋሰስ ባለፈው ሳምንት አጽድቃለች፡፡ ዐዲሷ የተፋሰሱ ሀገር የወሰደችውን ርምጃ፣ የጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “ታሪካዊ” ሲሉ አድንቀዋል፡፡
በሌላ መጠሪያው “የኢንቴቤ ስምምነት” እየተባለ የሚታወቀው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነት፣ በደቡብ ሱዳን መጽደቁ፣ ስምምነቱ በተፋሰሱ ሀገራት ተግባራዊ ሊኾን የሚችልበትን በቂ ድጋፍ የሚያስገኝ ነው፡፡
በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፣ ደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር ኾና የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱን መፈረሟ፣ ስምምነቱ “ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝና ወደ ተግባር እንዲሸጋገር የሚያስችል ነው፤” ብለዋል፡፡
ዐሥራ አንዱም የተፋሰሱ ሀገራት የሚጋሩትን የናይል ወንዝ፣ “ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ለግብጽ እና ለሱዳን ብቻ ያከፋፍላሉ፤” በሚል የሚተቹትን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመሻር በዐዲስ ለመተካት ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱ ሐሳብ አመንጪዎች እና ግንባር ቀደም ተዋናዮች ከኾኑት ሰባት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት አንዷ የኾነችው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነት በደቡብ ሱዳን መጽደቁ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ነው፤” ሲሉ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በማኅበራዊ የትስስር ገጾቻቸው አወድሰዋል፡፡
የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነት በደቡብ ሱዳን መጽደቁ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ነው፤”
ስምምነቱ ለ11 ዓመታት ከዘለቀ ውይይት በኋላ፣ በ2002 ዓ.ም. (በአውሮፓውያኑ 2010) ግንቦት ወር ላይ በኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ኬንያ ሲፈረም፣ ብሩንዲ በቀጣዩ ዓመት ስድስተኛ ሀገር ኾና ፈርማለች፡፡ ከእነዚኽ ሀገራት መካከል ከኬንያ በቀር አምስቱ ስምምነቱን በየአገሮቻቸው ሲያጸድቁ፣ ደቡብ ሱዳን ስድስተኛዋ የስምምነቱ አጽዳቂ ሀገር ኾናለች፡፡
የናይል ተፋሰስ የውኃ ምንጭ የኾኑት የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት፣ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱ፥ “ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም” የሚለውን መርሕ የሚያሟላ መኾን እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ስምምነቱ፥ “የውኃ ደኅንነታችንንና ታሪካዊ ድርሻችንን ማረጋገጥ አለበት፤” የሚል አቋም ያላቸው ግብጽ እና ሱዳን በበኩላቸው፣ እስከ አሁን ስምምነቱን አልፈረሙም፡፡
ደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር በመኾን ስምምነቱን ማጽደቋን ተከትሎ፣ ከሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እስከ አሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡
ስምምነቱ በደቡብ ሱዳን መጽደቁን፣ “ዲፕሎማሲያዊ እመርታ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው፣ ይህም “በናይል ተፋሰስ ቀጣናዊ ትብብር ለማድረግ ባለን የጋራ ምኞት ጉልሕ ርምጃ ነው፤” ብለዋል።
ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡት በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፣ የደቡብ ሱዳን ውሳኔ፣ ከ11ዱ የተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ የስምምነቱን አጽዳቂዎች ቁጥር ወደ ስድስት በማድረስ ወደ ተፈጻሚነት እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል፡፡ ይህም፣ ግብጽ እና ሱዳን፣ በቅኝ ግዛት ስምምነቶች መሠረት አለን የሚሉትን ታሪካዊ የውኃ መብት ጥያቄ የሚያስቀር እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡
በአውሮፓውያኑ 1929፣ በግብጽ እና በብሪታኒያ መካከል የተፈረመው ስምምነት፣ ከቅኝ ግዛት ስምምነቶች አንዱ ነው፡፡ በናይል(ዓባይ) ወንዝ እና በተፋሰሶቹ ላይ የሚገነቡ ማንኛውም ግንባታዎች፣ “ያለግብጽ ይኹንታ እንደማይከናወኑ ይደነግጋል፤” ይላሉ ፕር. ያዕቆብ።
የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱ በአንጻሩ፣ የናይል ተፋሰስ ሀገራት እያንዳንዳቸው በየግዛታቸው ውስጥ የናይል ወንዝን ውኃ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በኾነ መንገድ የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይገልጻል፡፡ ስምምነቱ፣ በስድስት ሀገራት
በተፈረመባቸውና በአምስቱ ከጸደቀ በኋላ ባሉ የተለያዩ ጊዜያት የግብጽ ባለሥልጣናት በሰጧቸው አስተያየቶች፣ ምንም እንኳን አገሪቱ የስምምነቱን በርካታ አንቀጾች ብትቀበልም፣ “ለአወዛጋቢ ጉዳዮች እልባት የሚሰጥ አይደለም በማለት” በተቃውሞዋ መቀጠሏን ገልጸዋል፡፡
ይኹን እንጂ፣ ስምምነቱ በስድስት ሀገራት መፈረሙን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መኾኑን የሚገልጹት የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ ፕር. ያዕቆብ አርሳኖ፣ ግብጽ እና ሱዳን አለመፈረማቸው ወደ ኋላ ሊመልሰው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት፣ አባል ሀገራት፣ በናይል ተፋሰስ ውኃ ላይ በሚሠሯቸው ግንባታዎች ምክንያት ቅሬታዎች ቢነሡ፣ ስምምነቱ መጽደቁን ተከትሎ በሚቋቋም የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እልባት እንደሚሰጠውም አስረድተዋል፡፡
በትብብር ማኅቀፉ ስምምነት ላይ፣ በላይኛው የተፋሰሱ ሰባት ሀገራት እና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ግብጽ እና ሱዳን መካከል መግባባት ካልተደረሰባቸው ነጥቦች መካከል፣ “በሌሎች የናይል ተፋሰስ ሀገራት የውኃ ደኅንነት ላይ ጉልሕ ተጽእኖ አለማሳደር” የሚለው አንቀጽ 14(ለ) ዋናው ነው፡፡
ይህ አንቀጽ “በሌሎች የተፋሰስ ሀገራት የውኃ ደኅንነት፣ እንዲሁም የአሁን አጠቃቀምና መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር” በሚል እንዲተካ ግብጽ ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡
የናይል የሚኒስትሮች ምክር ቤት በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም. በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኪንሻሳ ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአንቀጽ 14(ለ) ላይ የተመለከተው ጉዳይ፣ በናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን እልባት እንዲሰጠው ወስኗል፡፡
- ቪኦኤ ዜና
የናይል ወንዝ በውድቅዳቂ ቆሻሻ ተሞልቷል
በአህጉሪቱ ረዥሙ መሆኑ የሚነገርለት እና አሥራ አንድ አገሮችን አቋርጦ የሚፈሰው የናይል ወንዝ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቁጥሩ ከ200 ሚሊዮን በላይ ለሚደርስ ሕዝብ ዘላቂ የሕይወት ዋስትና ይሰጣል። ይሁን እንጂ ከወንዙ የላይኛው ተፋሰስ አካባቢዎች የሚታየው እና እያደርም እየጨመረ የመጣው የሰዎች እንቅስቃሴ የወንዙን ሥነ-ምህዳር ለአደጋ ማጋለጡ ተዘግቧል።
ሺላ ፖኒ ከደቡብ ሱዳኗ ጆንግሌይ ግዛት ቦር ያደረሰችንን የዚህን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
ያለስምምነት በተጠናቀቀው የሕዳሴ ግድብ ድርድር ግብጽ የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላት ተገለጸ
በዐዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት የተካሔደው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አራተኛው ዙር ድርድር፣ ያለስምምነት እንደተጠናቀቀ፣ ትላንት ያስታወቁት ኢትዮጵያ እና ግብጽ፣ ለውጤት አልባነቱ አንዳቸው ሌላቸውን ወንጅለዋል፡፡
ግብጽ፥ “ውይይቱ ያልተሳካው ኢትዮጵያ ምንም ዐይነት ስምምነት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመኾኗ ነው፤” ስትል፤ ኢትዮጵያም በበኩሏ፣ “የስምምነቱን መንገድ የዘጋችው ግብጽ ናት፤” ብላለች፡፡
በድርቅ ወቅት የሚኖረው የውኃ አያያዝ እና አለቃቀቅ፣ በድርድሩ ከፍተኛ ልዩነት የታየበት ጉዳይ እንደነበረ፣ የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ዶር. ስለሺ በቀለ ገልጸዋል፡፡
ግብጽ፣ “ከዚኽ በኋላ ድርድሩን የመቀጠል ፍላጎት የለኝም፤” እንዳለች የገለጹት አምባሳደር ስለሺ፣ የአፍሪካ ኅብረት ዳግም ወደ አደራዳሪነቱ ሊመለስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን፣ በዐዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ያካሔዱት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር ድርድር፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ያለስምምነት መቋጨቱን ያስታወቁት ኢትዮጵያ እና ግብጽ፣ ለውጤት አልቦነቱ እርስ በርስ ተወነጃጅለዋል፡፡
ያለፉት አራት ዙር ድርድሮች የተካሔዱት፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤል-ሲሲ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት እና አለቃቅ ዓመታዊ ክዋኔ ላይ፣ በአራት ወራት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ እንዲደረስ፣ በ2015 ዓ.ም. ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በተስማሙት መሠረት ነው፡፡
ይኹንና፣ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ሲካሔድ የቆየው የግድቡ ድርድር፣ በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም ላይ ከተቋረጠ በኋላ፣ በሦስቱ የተፋሰሱ ሀገራት መካከል፣ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ፣ በካይሮ እና በዐዲስ አበባ በተደረጉ የአራት ዙር ድርድሮች ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡
ለድርድሮቹ ፍሬያማ አለመኾን፣ ኹለቱ ሀገራት ባወጡት መግለጫ እርስ በርስ ተወቃቅሰዋል፡፡
የግብጽ የውኃ ሀብት እና መስኖ ሚኒስቴር፣ “ውይይቱ ያልተሳካው፥ ኢትዮጵያ ምንም ዐይነት ስምምነት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመኾኗ ነው፤” ሲል ከሷል፡፡
ስምምነት ላይ ላለመደረሱ፣ ግብጽን ተጠያቂ የምታደርገው ኢትዮጵያም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ፣ “ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቧ በመቀጠል፣ ወደ መግባባት የሚወስደውን መንገድ ዘግታለች፤” ስትል ወቅሳለች።
የሦስትዮሽ ድርድሩ ሲካሔድ የነበረው፣ 16 አንቀጾች ባሉት የጋራ መደራደሪያ ሰነድ ላይ በመመሥረት ሲኾን፣ ከፍተኛ ልዩነት የታየውም፣ በድርቅ ወቅት በሚኖረው የውኃ አያያዝ እና አለቃቀቅ ላይ ትኩረት በአደረገው አንቀጽ እንደኾነ፣ የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶር.) ድርድሩን አስመልክተው፣ ዛሬ ረቡዕ፣ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ልናስኬድ የቻልነው እስከ ስድስተኛው ክፍል ነው ነው። ስድስተኛው ክፍል ላይ ደግሞ ልዩነት አለ፡፡ ይሄም የድርቅ ሁኔታን የሚያመላክተው የውሃ አያያዝና አለቃቅ ጉዳይ ነው፡፡”
“ልናስኬድ የቻልነው እስከ ስድስተኛው ክፍል ነው ነው። ስድስተኛው ክፍል ላይ ደግሞ ልዩነት አለ፡፡ ይሄም የድርቅ ሁኔታን የሚያመላክተው የውሃ አያያዝና አለቃቅ ጉዳይ ነው፡፡” ያሉት ዶር. ስለሺ በዚህ ላይ መግባባትና መቀራረብ ስላልተቻለ፣ ስድስት ሰዎች ያሉበት የባለሞያዎች ቡድን ጉዳዩን እንደገና እንዲመለከት ሁለት ሰዎች መወከላቸውን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ የተወከሉት ሰዎች ደግሞ ከሁለቱ ቀናት የሚኒስትሮቹ ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ መወያየታቸውን አምባሳደር ስለሺ ጨምረው አስረድተዋል።
ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅት በሚለቀቀው የውኃ መጠን ላይ፣ በተደራዳሪዎቹ ሀገራት መካከል የቁጥር ልዩነቶች መኖራቸውን፣ አምባሳደር ስለሺ ጠቅሰዋል፡፡ በውኃው የክፍፍል መጠን ላይ ስምምነት በሌለበት ኹኔታ፣ ከታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በተቃራኒ ኢትዮጵያ፣ ቋሚ ቁጥር መቀመጥ የለበትም፤ የሚል አቋም እንዳላት፣ ዋና ተደራዳሪው አብራርተዋል፡፡
“ይሔን ቁጥር ስንሰጥ የኢትዮጵያን የወደፊት የመልማት ዕድል በሚገድብ መልኩ ሳይኾንን፣ የትብብር ስለሆነ ያንን ሊያስተካክል የሚችለው ሁላችንም የውሃ መብት ክፍፍላችን ሲታወቅ በዛ ስሜት እንሠራ።አን። እስከዛው መረጃ እየተለዋወጥን መቀጠል አለብን የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ ይሔ ደግሞ ፍትሐዊነት ነው፡፡ ሕዳሴ ግድብን ብቻ ስለሠራን ልማት አናቆምም፡፡ ከላይ የምንሠራቸው ግድቦች የውሃ ጉዳይ በኛ ድርሻ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ አሁን ያ ድርሻ የተቀመጠ ስላልሆነ በድርድር ውስጥ ለዚህ ዓይነት ችግር አጋልጦናል” ያሉት አምባሳደር ስለሺ ኢትዮጵያ፣ “ግትር አቋም ይዛለች፤” በሚል ግብጽ የምታቀርበውን ውንጀላም አስተባብለዋል፡፡
“ድርቅ ቢከሰት፣ ተፈጥሮ ከምትሰጠው በላይ ውሃ ጨምሮ ከመስጠት ሌላ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ከዛ በላይ መፍትሔ የለም፤ ቢኖር እነሱም ያቀርቡት ነበር፡፡” ያሉት ዋና ተደራዳሪው፤ “የሚፈለገውን መፍትሔ አስቀምጠናል፡፡ ነገር ግን እኛ ሀገር ላይ ጉዳት በሚያስከትል፣ ወይም ቀደም ሲል አለን በሚሉት የውሃ ኮታ መሰረት፣ ውሃውን ሙሉ በሙሉ ከተካፈሉ በኋላ ኢትዮጵያ ይሄን አረጋግጣ እንድትሰጣቸው የመፈለግ አካሔድ የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ ትክክለኛም አይደለም፤ እኛ ሀገር ሊያሰቅል ይችላል፡፡ የትም ሀገር ቢሆን ሃብቱን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ አይሰጥም፡፡ እንደላይኛው ተፋሰስ እኛ ብቻችንን እንጠቀም አላልንም፡፡ ተካፍለን አብረን እንልማ የሚል አቋም ነው ያለን፡፡” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ በድርድር ሽፋን፣ በኣባይ ወንዝ ላይ ከቁጥጥር ውጭ የኾነ ባለቤትነት እንዳላት፣ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ይኹንታ ለማግኘት ብቻ መደራደርን መርጣለች፤” ያለው የግብጽ የውኃ ሀብት እና መስኖ ሚኒስቴር፣ “ግብጽ በዓለም አቀፍ ቻርተሮች እና ስምምነቶች መሠረት፣ በውኃዋ እና ብሔራዊ ደኅንነቷ ላይ ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ጥቅሟን የመከላከል መብቷ የተጠበቀ ነው፤” ሲልም አስጠንቅቋል፡፡
“ኢትዮጵያ በድርድር ሽፋን፣ በኣባይ ወንዝ ላይ ከቁጥጥር ውጭ የኾነ ባለቤትነት እንዳላት፣ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ይኹንታ ለማግኘት ብቻ መደራደርን መርጣለች፤”
ኢትዮጵያ በበኩሏ፣ በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር፣ በሦስቱ ሀገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር ያለመ እንጂ፣ “በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ የኢትዮጵያን መብቶች ለማስነጠቅ አይደለም፤” ብሏል። የግብጽ መግለጫ፣ “የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር እና የአፍሪካ ኅብረትን ድንጋጌ የሚፃረር” እንደኾነም ሚኒስቴሩ ተችቷል፡፡ ኢትዮጵያ፣ የውኃ ሀብቷን፥ “ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በኾነ መንገድ፣ የአኹንና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት መጠቀሟን ትቀጥላለች፤” ሲልም አክሏል፡፡
አምባሳደር ስለሺ በቀለ በዛሬው መግለጫቸው፣ በድርድሩ ላይ ግብጽ፣ “ነባሩን የቅኝ ግዛት ዘመን የውኃ ክፍፍል የሚያንጸባርቅ” ሐሳብ በተደጋጋሚ ከማንሣቷም በላይ፣ “ቀጣይ ድርድር የማድረግ ፍላጎት እንደሌላትም ይፋ አድርጋለች፤” ብለዋል፡፡ ይኹንና ቀጣይ የድርድሩ ሒደት፣ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ መጠን፣ ከ94 በመቶ በላይ መድረሱን የገለጹት ዋና ተደራዳሪው አምባሳደር ስለሺ በቀለ(ዶር.)፣ ተጨማሪ አምስት ተርባይኖችም፣ በዚኽ ዓመት ኀይል ማመንጨት ይጀምራሉ፤ ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
- ቪኦኤ ዜና
የሕዳሴው ግድብ ላይ ድርድር ዛሬ ተጀምሯል
ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እየገነባች ባለችው የህዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርጉትን አራተኛ ዙር ድርድር ዛሬ አዲስ አበባ ላይ መጀመራቸውን ኢትዮጵያን የሚወክሉት ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በ X ማኅበራዊ መድረክ ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል።
ሶስቱ ወገኖች ባለፈው መስከረም አዲስ አበባ ላይ ያደረጉት ሶስተኛ ዙር ድርድር ካለ ውጤት ተበትኖ እንደነበር ይታወሳል።
ድርድሮቹ በመደረግ ላይ ያሉት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና የግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደል ፋታህ አል ሲሲ፣ በኢትዮጵያ እየተገነባ ባለው የህዳሴ ግድብ ጉዳይ፣ በአራት ወራት ውስጥ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ባለፈው ሐምሌ ማስታወቃቸውን መሠረት አድርጎ ነው።
አራተኛው እና በአዲስ አበባ በመቀጠል ላይ ያለው ድርድር፣ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ድርድሮች እና ትናንት እሁድ በቴክኒካዊ ቡድኑ በተደረጉ ውይይቶች ላይ እንደሚመሠረት አምባሳደር ስለሺ ጨምረው አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የምትመራው ግድቡን በተመለከተ እ.አ.አ 2015 በተደነገገው የመርህ ስምምነት እንዲሁም በጋራ እና በእኩልነት ላይ በተመሠረተ አጠቃቀም መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
4.6 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀው ግድብ ፍላጎቷን ከግምት ውስጥ የማያስገባ ከሆነ፣ የናይልን ወንዝ ለግብርና እና 100 ሚሊዮን ለሚሆን ሕዝቧ የውሃ ፍጆታ የምትጠቀመው ግብጽ ትልቅ ስጋት እንደሚሆንባት ስትገልጽ ቆይታለች
አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባለመሆኑ፣ ግድቡ አስፈላጊ እንደሆነ ኢትዮጵያ በበኩሏ ትገልጻለች፡፡
አራተኛውን ዙር የግድቡ ሙሌት ባለፈው 2015 መጨረሻ ላይ እንዳጠናቀቀች ኢትዮጵያ ማስታወቋ አይዘነጋም።
መድረክ / ፎረም